በአርመኖች ላይ የተደረገው የዘር ማጥፋት ዕልቂትን እናስታውስ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም )

Posted by: admin    Tags:      Posted date:  April 25, 2015  |  No comment

 

በአርመኞች ላይ የተደረገው የዘር ማጥፋት ዕልቂትን እናስታውስ

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Prof-Alemayehu-G-Mariam-200x200

የጸሐፊው ማስታዋሻ፡ በአሁኑ ጊዜ ቱርክ እየተባለች በምትጠራው ሀገር ከ100 ዓመታት በፊት በዛሬው ሳምንት እ.ኤ.አ ሚያዝያ 24/1915 በአርሜኒያ ዜጎች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ፍጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ያ የዘር ፍጅት የኦቶማን ግዛት/Ottoman Empire ዋና መቀመጫ በነበረችው እና ኮንስታንቲኖፕል (እ.ኤ.አ በ1923 ኢስታንቡል ተብላ በተሰየመችው) ተብላ ትጠራ በነበረችው ከተማ ውስጥ በአርሜኒያ ምሁራን፣ የክርስትና ኃይማኖት እምነት ተከታዮች፣ የትምህርት ሰዎች፣ በጸሐፊዎች፣ በማህበረሰብ መሪዎች እና በሌሎች ታዋቂ በነበሩ የማህበረሰብ ስብስቦች ላይ ተጀመረ፡፡

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን ሀገራቸው አድርገው ይኖሩ በነበሩ አርሜናውያን ላይ እ.ኤ.አ በ1915 የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ፍጅት ለማስታወስ በሚል ይህንን ትችት እየጻፍኩ ያለሁት ጥቂት አርሜናውያን ኢትዮጵያን ሀገራቸው አድርገው ሲኖሩ የቆዩ በመሆናቸው ምክንያት አይደለም፡፡ እንደዚሁም በወጣትነት ዘመኔ ኢትዮጵያዊ አርሜናውያን የትምህርት ቤት ጓደኞች የነበሩኝ በመሆኑ ምክንያት አይደለም ይህንን ትችት እየጻፍኩ ያለሁት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተማሪዎች እና አርሜናውያን፣ የኢትዮጵያ አርሜናውያን ወይም ደግሞ የአርሜናውያን ቅርስ በመኖሩ ምክንያት አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአርሜናውያንን የዘር ማጥፋት ዕልቂት የማስታውስበት እንዲህ የሚል ቀላል እና ግልጽ የሆነ የማሳመኛ አመክንዮ አለኝ፡ በዓለም ላይ በሀያኛው ክፍለ ዘመን እ.ኤ.አ ሚያዝያ 24/1915 ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ዕልቂት እና ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ላለቁበት ሰይጣናዊ ድርጊት የዓለም ህዝብ ቁጣ ቢኖር ኖሮ፣ እንዲሁም ይህንን ዕኩይ ድርጊት በአርሜናውያን ህዝቦች ላይ በፈጸሙት ጭራቆች ላይ ተጠያቂነት ቢኖር ኖሮ፣ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 7/1994 ያ ጭራቃዊ ድርጊት በዚሁ ወር ከተፈጸመ ከ79 ዓመታት በኋላ ወደ 1 ሚሊዮን አካባቢ በሆኑ የሩዋንዳ ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ዕልቂት አይፈጸምም ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአርሜናውያን ላይ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ዕልቂት  የዓለም ህዝብ ቁጣውን ቢገልጽ ኖሮ፣ ያንን የመሰለ ጭራቃዊ ድርጊት በፈጸሙት ሰይጣኖች ላይ ተጠያቂነት ቢኖር ኖሮ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ቢወሰድባቸው ኖሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ያንን የመሰለ አሰቃቂ ዕልቂት ይፈጸማል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሂትለር ያንን ዕኩይ ድርጊት በመመልከት በፖላንድ እና በሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሀገሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለመፍጀት የሚያስችለው አድርጎ በመቁጠር እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞበታል፡፡ እ.ኤ.አ ሕዳር 24/1945 የለንደን ጊዜ/The Times of London የተባለው ጋዜጣ እ.ኤ.አ ሂትለር ነሀሴ 1939 ፖላንድን ከመውረሩ በፊት ያ እብሪተኛ አምባገነን ቆጥቋጭ የሆነ ንግግር አድርጎ እንደነበር ዘግቧል፡፡ ሂትለር እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “ጥንካሪያችን ያለው በእኛ ፍጥነት እና የጨካኝነት መጠን ነው…ደካማው የአውሮፓ ስልጣኔ ስለእኔ ስለሚያስበው ነገር ጉዳዬ አይደለም…ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ፣ እናም አንድ ቃል በመሰንዘር ትችት አቀርባለሁ የሚል ማንም ቢሆን ይገደላል… ስለሆነም ለጊዜው የእኔን ገዳይ ኃይሎች ብቻ ወደ ምስራቅ በማዝመት ያለምንም ርህራሄ ወይም ደግሞ ሀዘኔታ ሁሉንም የፖላንድ ዘሮችና እናቋንቋውንም የሚናገሩ ሁሉንም ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች እንዲገድሉ ልኪያቸዋለሁ፡፡ በአሁኑም ጊዜ አርሜናውያንን መፈጀት በመናገር ላይ ያለ ማን ነው?“ (አጽንኦ ተሰጥቷል፡፡)

የሂትለር ጥያቄ እንዲህ የሚል ቀላል መልስ አለው፡ ሁሉም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጨዋ ሰዎች ላይ ኢሰባዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጸምባቸው እና እ.ኤ.አ ከ1915-1923 በአርሜናውያን ህዝቦች ላይ ሲፈጸም የነበረው ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት የሚቃወሙ ሁሉ በመናገር ላይ ይገኛሉ። ደግሞም ሰው ለሰው ልጅ ተኩላ ነው የሚለዉን መርህ የሚቃወሙም  ስለ አርመኖች አልቂት ይናገራሉ;

የአርሜኒያ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ትስስር፣

በኢትዮጵያ እና በአርሜኒያ መካከል የነበረው ግንኙነት ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአክሱም ግዛት በኢትዮጵያ ከተመሰረተ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በኦቶማን ግዛት ስቃይ እና መከራ ይደርስባቸው የነበሩ ጥቂት የአርሜኒያ ቡድኖች ሽሽት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ነበር፡፡ ጥቂት የታሪክ ባለሙያዎች እንደሚሉት እ.ኤ.አ በ1895 በኦቶማኖች ይፈጸም በነበረው ዕልቂት ምክንያት በኢትዮጵያ የነበሩት የአርሜኒያ ማህበረሰቦች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቶ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት ዮሐንስ 4ኛ በኦቶማን ገዥዎች እንግልት እና ስቃይ ይደርስባቸው የነበሩት አርሜናውያን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መኖር እንደሚችሉ ግብዣ ያቀርቡ ነበር፡፡ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በአዲስ አበባ 50 አርመኖች ይኖሩ ነበር፡፡ አርመኖች፣ የወርቅ ማዕድን አንጥረኞች፣ ነጋዴዎች እና የስነህንጻ ባለሙያዎች እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ እንደሚቀርቡ ዘገባዎች ከሆነ እ.ኤ.አ በ1905 የአርሜኒያ-ታታር (አዘርባዣ) ዕልቂትን ተከትሎ በርካታ አርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይነገራል፡፡

እ.ኤ.አ በ1923 ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እየሩሳሌምን ጎበኙ፡፡ በእየሩሳሌም አርመኖች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ላይ በነበሩበት ጊዜ 40 አባላትን ያካተተ የሙዚቃ ቡድን ሙዚቃዎችን በማቅረብ ላይ እንዳለ ተመለከቱ፡፡ እነዚህ የሙዚቃ ቡድኑ አባላት በዘር ማጥፋት ፍጅት ወላጆቻቸውን ያጡ እንደነበሩ ተገነዘቡ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚያ ወላጅ አልባ ልጆች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው በመገንዘብ የጡት ልጅ በማድረግ ለማሳደግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ፈቃዳቸውን ገለጹ፡፡ ለዚህም ከአርመኖች ጳጳስ ፈቃድ አገኙ እና ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ ይዘዋቸው መጡ፡፡ እነዚህ ወጣት ወንዶች በኋላ “አርባ ልጆች“ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት የንጉሱ የሙዚቃ ተጫዋች ቡድን ሆኑ፡፡ የዚህ የሙዚቃ ቡድን መሪ የነበረው ኬቮርክ ናልባንዲያን ኢትዮጵያ ሆይ በሚለው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ ደስ ይበልሽ በሚል የተፈሪ የሙዚቃ ማርሽ ላይ የሚሳተፈውን የአርሜኒያን ወጣት ቡድን በማንቀሳቀስ ረገድ ትልቅ ዕውቅና የተሰጠው ሰው ነበር፡፡ ያ የሙዚቃ ቡድን እ.ኤ.አ ሕዳር 2/1930 አጼ ኃይለ ስላሴ የዘውድ ንግስ በዓላቸውን ሲያከብሩ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነበር፡፡ ያ ብሄራዊ የሙገሳ ሙዚቃ እ.ኤ.አ በ1974 ወታደራዊው አምባገነን መንግስት ስልጣን እስከሚይዝ ድረስ ያገለግል ነበር፡፡ (የዚያን የሙዚቃ ቡድን የመሳሪያ ቅንብር ሙዚቃ ለማዳመጥ እዚህ  ይጫኑ፡፡) የአርመኖች የመጀመሪያው ቡድን እና ልጆቻቸው ውጤታማ፣ ስኬታማ እና በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ባህላዊ ተግባራት ላይ በታማኝ ዜግነት ተሰማርተው ያገለግሉ ነበር፡፡

በታሪክ የኢትዮጵያ እና የአርመን ክስርትና እምነት ተከታዮች በዓለም ላይ 2ኛው የክርስትና እምነት ቤተክርስቲያን የምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አካል ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በአርመኖች እና በኢትዮጵያውያን መካከል የትምህርት ግንኙነትን በመፍጠር የእውቀት የልውውጥ መድረክ ተከፍቶ ነበር፡፡ “በአርሜኒያ የፊደላት ዕድገት ላይ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ“ በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መጽሔት (ቮል. 1፣ ቁጥር 1) ተዘጋጅቶ በቀረበ መጽሔት ላይ አየለ በከሬ እንዲህ በማለት የክርከር ጭብጣቸውን ያቀርባሉ፣ “የሁለቱን ሀገሮች የጽሁፍ ስርዓት በምንመረምርበት ጊዜ ልዩ የሆነ ምሁራዊ እና ባህላዊ ጥናቶችን ይገልጻል፡፡“

በርካታ የኢትዮጵያ አርመኖች እ.ኤ.አ በ1974 የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት ስልጣን በተቆናጠጠበት ጊዜ ንብረቶቻቸውን በመውረስ ከሀገር እንዲባረሩ ተደርገዋል፡፡ አብዛኞቹ ወደ ዩኤስ አሜሪካ እና ወደ ካናዳ ሄደዋል፡፡ 

ስለአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ፍጅት ውዝግብ እና ስለማይካደው እውነታ፣ 

እ.ኤ.አ ከ1915-1923 ባሉት ዓመታት ውስጥ በኦቶማን መንግስት በአርመኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞ ነበርን?

እ.ኤ.አ ከ1915-1923 ድረስ ባሉት ዓመታት መካከል በኦቶማን ቱርክ ስር በነበሩት አርመኖች ላይ ምንድን ነገር ነበር የተደረገው?

እ.ኤ.አ በ1915 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የኦቶማን ግዛት መፈረካከስ በሚጀምርበት ጊዜ የቱርክ አመራሮች በምስራቁ ግዛት የሚገኘው አናሳው የአርመን የክርስቲያን ህዝብ ከራሽያ ጋር በመቀላቀል እነርሱን ሊወጋቸው እንደሚችል ቱርኮች ስሌታቸውን ሰርተው ነበር፡፡ የቱርክ ባለስልጣኖች አስቀድሞ ለማጥቃት ዝግጅት በማድረግ አርመኖችን ማጋዝ እና መጠነ ሰፊ የሆነ ግድያን ጨምሮ ስልታዊ የሆነ የማሰቃየት ድርጊት እንዲፈጸምባቸው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በኦቶማን ቱርኮች ወታደሮች እና ፖሊሶች አማካይነት ወደ በረሀዎች ፈጥኖ በመድረስ፣ በረሀብ በማሰቃየት እና ግድያን በመፈጸም ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚን የአርመን የጎሳ ዝርያ ያላቸው ዜጎች ያለቁ መሆኑ ይገመታል፡፡ ሌሎች ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ በራሽያ፣ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና ሌሎች የአርሜኒያ ዲያስፖራን በመመስረት ስደተኛ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1915 በቱርክ ውስጥ የነበረው የአርመን ህዝብ በኦቶማን መንግስት ላይ ወይም ደግሞ ሩሲያን ደግፎ በማመጽ በቱርክ እና በአጋሯ በጀርመን ላይ አምጾ ስለመነሳቱ በዋቢነት ሊቀርብ የሚችል ታሪካዊ ማስረጃ የለም፡፡

የቱርክ መንግስት ለዘመናት ያህል በቱርክ ውስጥ የሚገኙ አርመኖች የዘር ፍጅት ዕልቂት  ወይም ደግሞ የዕልቂት ዘመቻ ሰለባ መቸውንም ጊዜ አልነበሩም በማለት ሙልጭ ያለ ክህደት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እንደ የቱርክ መንግስት ዘገባ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት አርመናውያን ያለቁት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ሲያደርጉት በነበረው አጭር ውጊያ ወይም ደግሞ በአንደኛው የዓለም ጦርነት አሰቃቂ ዕልቂት አማካይነት ነው ይላል፡፡ የቱርክ መንግስት እንደማንኛውም ጦርነት ሁሉ ጥቂት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች ተካሂደው እንደነበር አምኖ ሆኖም ግን በዘር ማጥፋት ዘመቻ አማካይነት ምንም ዓይነት የአርመን ሰው እንዳልተገደለ ሙልጭ አድርጎ የክህደት ቃል ሰጥቷል፡፡

የቱርክ መንግስት ክህደት በእውነታ ላይ እና የሕግ ጭብጥን መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ አይደለም፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪክ የቱርክ አምባሳደር የሆኑት እንደ ናቢ ሴንሶይ አባባል ከሆነ የጅምላ መቃብሮች እና በገፍ በአንድ ላይ ተቀብረው የተገኙት ታሪካዊ የአርመኖች የሰው ቅሬተ አጽሞች  ሁኔታ በቀላሉ “የጦርነትን አሰቃቂነት” የሚያመላክት ማስረጃ እንጅ አርመኖች በቱርኮች ለመፈጀታቸው የሚያመላክት ምንም ዓይነት ነገር የለም ብለዋል፡፡ ሴንሶይ  እ.ኤ.አ ከ1915 ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የአርመን ህዝብ የማለቁ ሁኔታ ማጋዝ በሚደረግበት ጊዜ እና ወደ ማጋዝ በሚሄድበት ጊዜ እንደሆነ በመግለጽ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በአርመኖች ላይ የተቀነባበር ግድያ አልነበረም፣ ሆኖም ግን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ምክያንት በርካታ ሰዎች ያለቁ የመሆናቸውን እውነታ ጨምሮ አሰቃቂ ነገሮች ተፈጽመዋል፡፡“ የሴንሶይ የዘር ማጥፋት ዕልቂት አልተፈጸመም ዓይነት የህግ ጭብጥ ክርክር በተሳሳተ ማዕዘን ላይ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ለሴንሶይ  በአርመኖች ላይ የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ዕልቂት ወይም ደግሞ ግድያ በእራሱ የዘር ማጥፋት ዕልቂት መሆኑን አያረጋግጥም፣ ይልቁንም ይኸ የሚያሳዬው ጉዳይ ቢኖር ከፍተኛ ብዛት ያለው ሰው ማለቁን ነው፡፡ ሴንሶይ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፣ “ዋናው ቁም ነገር ሙከራው ነው፡፡ ግድያው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በሁለቱም ወገኖች በኩል የተፈጸመ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን የዘር ማጥፋት ፍጅት ይዞ ከሆነ ይኸ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይኸ የሕግ ቃለ ነው እናም አንዲሁ በቀላሉ ጥቅም ላይ የሚውል ነገር አይደለም፡፡ የአርመንን ህዝብ በአጠቃላይ ወይም ደግሞ በተናጠል የመውረር ዓላማ የለም፡፡“ በሴንሶይ የክርክር ጭብጥ ላይ ድብቅ ሆኖ የሚታየው ነገር እ.ኤ.አ በ1915 በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የዘር ማጥፋ ወንጀል አልነበረም፣ እናም እንደ ሕግ ቱርክ የምትባል ሀገር ምንም ዓይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል አልፈጸመችም የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡

ራፌል ለምኪን ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል ለመግለጽ በአይሁዶች እና በሌሎች ላይ በናዚ የተፈጸመ ስልታዊ የሆነ የጅምላ ግድያ በማለት ያያይዙታል፡፡ ለዘመናት የቱርክ መንግስት እ.ኤ.አ ከ1915-1923 ባሉት ዓመታት ውስጥ በአርመኖች ላይ የተካሄደውን ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል በጥቅም ላይ ላለማዋል ሽንጡን ገትሮ በመከላከል ላይ ይገኛል፡፡ በዚያን ጊዜ የተፈጸመውን ነገር ለመግለጽ ዘር ማጥፋት ከሚለው ቃል በስተቀር ማንኛውንም ነገር ይቀበላሉ፡፡ ዘር ማጥፋት የሚለው ቃል እ.ኤ.አ በ1948 በዘር ማጥፋት የተባበሩት መንግስታት በጸደቀው ሰነድ ላይ ተካትቶ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባሉ ዓለም አቀፍ የሕግ መስፈርቶች የዘር ማጥፋት የሚለው ቃል ለመፈጸም ባቀዱ፣ ባቀነባበሩ፣ ትዕዛዝ በሰጡ፣ በተገበሩ፣ ወይም ደግሞ እገዛ ላደረጉ እና በእቅድ፣ ዝግጅት ወይም ደግሞ በአፈጻጸም ጊዜ ሆን ተብሎ ሙሉ ለሙሉ ወይም ደግሞ በከፊል ለማጥፋት እንዲሁም በብሄራዊ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ ወይም ደግሞ በኃይማኖት፣ በቡድን፣ ወዘተ በመደራጀት የሚሰፋ ቃል ይሆናል፡፡ በእርግጥ ሴንሶይ በሕግ ትንታኒያቸው ላይ ስህተት ሰርተዋል፡፡ በአጠቃላይ በሕጉ ላይ ስለሚናገሩት የዕቅድ ድርጊት ሆን ተብሎ አንድን ቡድን በጎሳ፣ በዘር፣ ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ለማጥቃት ወይም ደግሞ ትንበያ ለመስጠት እና መጥፎ ነገር በማድረግ  ለመውረር ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል በትክክል ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ ያህል በአንድ በተሰበሰበ ህዝብ ላይ ጥይት በመተኮስ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ያለበት በት ዉስጥ ተኩስ ከፍቶ የሰው ነፍስ ቢጠፋ ግድያ አልተፈጸመም ማለት አይቻልም። 9 ሺ አርመናውያንን ለመግደል የማዘዣ ወረቀት አልወጣም ስለዚህ  በ9 ሺሺ አርመናውያንን  የተገደሉና ወደ ወንዝ በጅምላ የተጣሉት የዘር ጥፋት አይደለም ማለት አይቻልም።   በእርግጥ ያ ድርጊት መተግበሩን ለመተንበይ አስፈላጊነት የለውም ምክንያቱም የኦቶማን መንግስት አናሳ የሆኑትን የአርሜናውያንን ህዝቦች የክርስትና እምነት ተከታዮች በተገኘው ማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ በማስወገድ የጎሳ እና የኃይማኖት ማጽዳት ሲያካሂድ እንደነበር ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ የሰነድ እና የቃል ምስክርነት ማስረጃዎች ነበሩ፡፡

ማስተባበያ ሊቀርብባቸው የማይችሉት የአርመናውያን የዘር ማጥፋት ፍጅቶች ምንድን ናቸው?

እ.ኤ.አ ከ1915-1923 ባሉት ጊዚያት ውስጥ በቱርክ ውስጥ በነበሩት አርሜናውያን ላይ በእርግጠኝነት ምን እንደተደረገ ለመወሰን ማንም ሰው ቢሆን የሰነድ ማስረጃዎችን ነጻ በሆነ መልኩ መሰብሰብ እና ታሪካዊ እውነታዎችን መመርመር አለበት፡፡ ተመዝግቦ የሚገኘው የዘር ማጥፋት ፍጅት ድርጊቱ እጅግ ግዙፍ የሆነ ማስረጃ የሚገኝበት ነው፡፡ እ.ኤ.አ ነሀሴ 4/1915 የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “9 ሺ አርመናውያን እንዲያልቁ ተደርገው ወደ ቲሪስ ወንዝ እንዲጣሉ ተደርገዋል፣“ በጥይት ተደብድበው ወደ ወንዙ ተጥለዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ ነሀሴ 18/1915 የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ ”አርሜናውያን ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ ወደ በረሀ ይላካሉ፣ ቱርኮች ሁሉንም ህዝብለመጨረስ ባዘጋጁት ዕቅድ ላይ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡“  (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡) ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ ነሀሴ 20/1915 የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ  የሚል ዘገባ  አውጥቶ ነበር፣ “በአንድ መንደር 1000 ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች ከእንጨት በተሰራ ቤት ውስጥ እንዲቆለፍባቸው ተደርጎ ቤቱን በእሳት እንዲቃጠል በማድረግ እንዲያልቁ ተደርገዋል፡፡“ እ.ኤ.አ ነሀሴ 27/1915 የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ የሚል ዘገባ አስነብቦ ነበር፣ ”ቱርኮች የአርሜናውያንን ከተማ  በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡“ እንደዚሁም ደግሞ የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እ.ኤ.አ መስከረም 24/1915 የዩኤስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ በአርሜናውያን ውስጥ በነበሩት የኮንሱላር ኃላፊዎች አማካይነት በትንሿ ኢስያ ባገኙት በቂ እና ዝርዝር መረጃ መሰረት የአርሜኒያ የክርስትና እምነት ተከታዮች በቱርክ እና በኩርዶች ይፈጸሙባቸው የነበሩትን የፍርሀት፣ የእልቂት እና ተስፋ የመቁረጥ የጭካኔ አያያዞች ትረካዎችን ያቀርቡ እንደነበር ግልጽ አድርጓል፡፡ እነዚህ ዘገባዎች ሁሉ ለህዝብ ይፋ አልተደረጉም ነበር፡፡ የቀረቡት ሁሉም ዘገባዎች በአርሜኒያውያን ላይ በተለይም ደግሞ 90 በመቶ አርሜኒያውያን በሆኑት በግሪጎሪያን ቤተክርስቲያን ላይ የጦርነት ፍጅት ይፈጽሙ እንደነበር በግልጽ ያመላክታሉ፡፡ የቱርክ መንግስት ገና ከመጀመሪያው አርሜኒያውያንን ያግዝ ነበር፣ ሆኖም ግን በጊዜ ሂደት በዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ሞርገንዛው ከተሾሙ በኋላ የኦቶማን መንግስት የካቶሊክን እና የፕሮቴስታንት ኃይማኖት እምነት ተከታዮችን እንዳያካትት ትዕዛዙ እንደገና እንዲሻሻል ማጋገጫ ሰጠ፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)   

እ.ኤ.አ በ1915 ብቻ በአርሜናውያን የዘር ማጥፋት ዕልቂት ላይ በኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ከ194 በላይ ዘገባዎች ቀርበዋል!

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የአርሜናውያንን የዘር ማጥፋት ፍጅት ሙሉ በሙሉ ተገንዝቦት ነበር፣ ሆኖም ግን ለጉዳዩ ምንም ዓይነት ትኩረት ሳይሰጥ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ዝም ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ የዩናናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ሞርገዛው እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፡

ሁሉም የሰው ልጅ ዘር ታሪኮች እንደዚህ ያለ በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ አስፈሪ ክስተትን አስተናግደው አያውቁም፡፡ እነዚህ እ.ኤ.አ በ1915 በአርሜናውያን ዝርያ ላይ በመፈጸም ላይ ያሉት እልቂቶች እና ስቃዮች ባለፉት ጊዚያት በምድር ላይ ከተፈጸሙት እልቂቶች እና ስቃዮች ጋር ሲነጻጸሩ ምንም ያህል ውኃ የሚቋጥሩ ሆነው አይገኙምየቱርክ ባለስልጣኖች እንደዚህ ያሉትን የማጋዝ ትዕዛዞች ሲሰጡ ለሁሉም የሰው ዘር የሞት ማረጋገጫዋስትና ነበር የሰጡት፣ እንደዚሁም ደግሞ ይህንን ጉዳይ አሳምረው ያውቁት ነበር እናም ከእኔ ጋር በሚያደርጓቸው ንግግሮች ሁሉ እውነታውን ለመደበቅ የተለዬ ሙከራ ሲያደርጉ አይታዩም ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በአርሜናውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት ላይ ሊካድ በማይችል እውነታ ላይ ክህደት መፈጸም፣

ቱርክ በአርሜናውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት ላይ ጠንካራ የሆነ አወዛጋቢ ሁኔታ ብታቀርብም እንኳ የድርጊቱ የመፈጸም እውነታ በበርካታ ሀገሮች ማለትም ካናዳን፣ ጀርመንን፣ ግሪክን፣ ጣሊያንን፣ ፖላንድን፣ ሩሲያን፣ ስዊድንን፣ ስዊዘርላንድን እና የሮማን ጳጳስ ጨምሮ በሁሉም ዘንድ በሚገባ ይታወቃል፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች አህጉራዊ መንግስታትም (አህጉራዊ ፓርላሜንቶች በተለይም ሀገሮች) እንደዚሁም አርመኖች ታላቁ እልቂት እያሉ ይጠሩት የነበረውን የዘር ማጥፋት ፍጅት በሚገባ ያውቁት ነበር፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ከ50ዎቹ ግዛቶች 43ቶቹ በአርሜናውያን ላይ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ፍጅት እውቅና በመስጠት እያንዳንዱ ግዛት አዋጅ አውጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ  2010 የዩኤስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ቃል አቀባይ እ.ኤ.አ በ1915 የተፈጸመውን እልቂት የዘር ማጥፋት ድርጊት የሚል እውቅና ሰጥቶታል፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 19/2008 የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር እና ዕጩ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ብለው ነበር፣

እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የምክር አባልነቴ/ሴናተርነቴ ከአርሜኒያ አሜሪካን ማህበረሰብ ጎን በመቆም ለአርሜናውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት እውቅና እንድትሰጥ ለቱርክ ጥሪዬን አቀርባለሁ…እንደ ምክር ቤት አባል የአርሚኒያን የዘር ማጥፋት የውሳኔ መግለጫ (H.Res.106) ማለፍ እንዲችል እንደምደግፍ እና እንደ ፕሬዚዳንት ለአርሚኒያ የዘር ማጥፋት ዕልቂት ዕውቅና እሰጣለሁ፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

የባራክ ኦባማ ሌሎች ተቆጥረው የማያልቁ የተሰበሩ ቃል ኪዳኖች፣

ባለፉት አስርት ዓመታት የቱርክ መንግስት በአርሜኒያ ምንም ዓይነት የዘር ማጥፋት ፍጅት እንዳልተካሄደ ለማሳመን ማቋረጫ የሌለው የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በእራሱ ህዝብ ላይ በሀገር ውስጥ የተሳካለት ይመስላል፡፡ በቅርቡ የኢኮኖሚክስ እና የውጭ ፖሊሲ ጥናት ማዕከል/Center for Economics and Foreign Policy Studies የተባለ የኢስታንቡል የጥናት ድርጅት ባጠናው ጥናት መሰረት 9 በመቶ የቱርክ ህዝብ የቱርክ መንግስት ያደረገው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን አምኖ ድርጊቱን የፈጸመባቸውን ሀገር ህዝቦች ይቅርታ እንዲጠይቃቸው አሳስቧል፡፡

የቱርክ መንግስት በአርመን ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ድርጊት እንዳልፈጸመ ለመካድ እያደረጋቸው ያሉት ዓለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ጥረቶች ከፍተኛ ቢሆኑም በአብዛኛው ስኬታማ አልሆኑም፡፡

ሁሉንም የማታለል ዘዴዎች ሁሉ ሞክረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 እንደወጣው ዘገባ ከሆነ ቱርክ ለዲኤልኤ ፓይፐር/DLA Piper 1.2 ሚሊዮን ዶላር ለዓመቱ የከፈለ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ 750,000 ለሊቪንግስተን ቡድን/Livingston Group ለአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ፍጅት እውቅና እንዳይሰጥ ለሚወተውቱ እና በአሸናፊነት ለመውጣት በሚል ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ምክር ቤት/ ኮንግረስ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሰነድ እንዳይጸድቅ ዲኤልኤ ፓይፐር/DLA Piper የተባለው ወትዋች አሸናፊ ለመሆን ሲጫወት የነበረውን ሚና በርካታ ኢትዮጵያውያን ያስታውሳሉ፡፡ (እ.ኤ.አ በ2007 ዲኤልኤ ፓይፐር/DLA Piper የተባለውን ወትዋች ለመሞገት አዘጋጅቸው የነበረውን ባለ16 ገጽ ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ  ይጫኑ፡፡ የአርሜናውያን ብሔራዊ ኮሚቴ ዳይሬክተር የነበሩት አራም ሀምፓሪያን ቱርክ ለገጽታ ግንባታዋ ጎጂ መሆኑን ብታውቅም እንኳ የቱርክን የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 301 ዲኤልኤ ፓይፐር/DLA Piper ከቱርክ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በመውሰድ በክርክሩ ጉዳዮች ላይ ለመከላከል እና የኮንትራክት ስምምነቱን ለማሸነፍ ባደረጉት ጥረት በተለዬ መልኩ ከታላቅ ችግር ላይ ወድቀው ነበር፡፡ ከአርሜኒያ ዴሞክራሲያዊ ባህል ውጭ የሆነው ይኸ መስፈርት ቱርክነትን ለመዘለፍ የተደረገው ንግግር እና ወንጀል ነው በማለት የመናገር ነጻነትን ለመጨቆን ከቱርክ መንግስት ጥረቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ሆኗል፡፡

የቱርክ መንግስት ስለአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ፍጅት በድፍረት በሚናገረው ላይ ሁሉ ሀሰት እና ጎጅ የሆነ ነገር በመናገር፣ በማስቸገር፣ እና ማንንም ጥላሸት በመቀባት ምንም ዓይነት ያባከነው ጥረት የለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ፖፕ ፍራንሲስ እ.ኤ.አ በ1915 በአርሜናውያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ፍጅት ወንጀል በማለት ጠርተውታል፡፡ በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል፣ “ጭራቃዊነትን መደበቅ ወይም ደግሞ መካድ በቁስል ላይ ምንም ዓይነት ፋሻ ሳያስሩ ደሙ ያለምንም የመከላከል ጥረት እንዲሁ እንዲፈስ መፍቀድ ማለት ነው፡፡“ ፖፕ ኦቶማን ቱርኮች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑትን አርሜናውያንን የመፍጀታቸውን ጉዳይ የዓለም ህዝብ መርሳት የለበትም በማለት ጩኸታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡

የፖፕ ፍራንሴ መግለጫ የቱርክን መንግስት ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ አደረገው…የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመት ዳቩቶግሉ በፖፕ ፍራንሲስ ላይ የጭቃ ጅራፋቸውን በማጮህ እንዲህ በማለት ጥላሸት መቀባት ጀመሩ፡፡ “ህገወጥ የሆነ ጭራቃዊነት ከፊት ለፊታችን ቆሞ ይታያል…እናም በአሁኑ ጊዜ ፖፕ እና እነዚህ ሸፍጦች ተቀላቅለውታል…በታሪክ ሀገራችን እንድትዘለፍ አንፈቅድም፣ ቱርክ በታሪካዊ ንትርክ ውስጥ ተገድዳ እንድትገባ በፍጹም አንፈቅድም፡፡“ አምባሳደራቸውን ከቫቲካን እንደገና ጠሯቸው፡፡

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  የሆኑት ሜቭሉት ካቩሶግሉ ንቀትን የሚያሳዩ ባለስልጣን ናቸው፡፡ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ከማንኛውም ዓይነት የህግ ወይም ደግሞ ታሪካዊ እውነታ ያፈነገጠውን የፖፕን መግለጫ ለመቀበል አይቻልም…የኃይማኖት ባለስልጣኖች መሰረተቢስ የሆነ ውንጀላን በማራመድ የበቀል እና የጥላቻ መቀፍቀፊያ ቦታዎች አይደሉም፡፡“

የአውሮፓ ጉዳዮች የቱርክ ሚኒስትር የሆኑት ቮልካን ቦዝኪር ከስነምግበር ውጭ በሆነ መልኩ እና ባልተረጋጋ የስነ ልቦና መንፈስ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ፖፕ ፍራንሲስ አርጀንቲናዊ ነው…አርጀንቲና የተባለችው ሀገር የአይሁዳችን ዕልቂት ፈጻሚ የናዚ አሰቃዮችን ግልጽ በሆነ መልኩ ለፍትህ እንዲቀርቡ በበላይነት የመራች ሀገር ናት…በአርጀንቲና ያሉ የአርመን ዲያስፖራዎች የመገናኛ ብዙሀንን እና የንግድ ስርዓቱን ተቆጣጥረውታል፡፡“ እንዴት ያለ እንቆቅልሽ የሆነ አስገራሚ ነገር ነው! ቦዝኪር ከአይሁዶች እልቂት ጋር ተመሳሳይ ነው የሚሉትን ሰዎች በመለየት እና ጥላሸት በመቀባት ፈጣን ነበሩ፣ ሆኖም ግን የአርመናውያንን የዘር ማጥፋት ፍጅት የሚያነሱትን ሰዎች ከፍተኛ በሆነ መልኩ ይተቿቸዋል፡፡ ቦዝኪር ምናልባትም እንዲህ የሚለውን የቆዬ አባባል አልሰሙትም ይሆናል፣ “አመልካች ጣትህን በሰዎች ላይ ስትቀስር ሌሎቹ ሶስቱ ጣቶችህ ወደ አንተ እንዲያመለክቱ አስተውል“

የቱርክ ፕሬዚዳንት የሆኑት ርሴፕ ቲ. ኢርዶጋን የጥቃቱ ሰለባዎችን በማውገዝ የአርሜኒያውያንን የዘር ማጥፋት ፍጅት ጨዋታ ተጫውተዋል፡፡ በመሰረታዊ ነገር የዓለም ህዝብ ስለአርሚኒያውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት ምን እንደሚያስብ ደንታ ሳይሰጡ ተናግረዋል፡፡ በአንዱ ጆሮ ገብቶ በሌላኛው ይወጣል በማለት እንዲህ ብለው ነበር፣ “የአርሜናውያን ዲያስፖራ እ.ኤ.አ በ1915 ምዕተ ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት አስቀድሞ ቀደም ሲል ተካሄደ በተባለው የዘር ማጥፋት ፍጅት በዓለም አቀፍ ዘመቻ በቱርክ ላይ የጥላቻ መንፈስ እንዲሰርጽ ጥረት እያደረገ ነው…ሀገራችን ባለፉት ከ100  እስከ 150 ዓመታት ውስጥ ምን እንዳደረገች አርሜናውያን እየሄዱበት ካለው በበለጠ አስቸጋሪ በሆኑ ነገሮች ላይ አልፈናል፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ የቱርክ ዜግነት ያላቸው ወይም ደግሞ የሌላቸው 100,000 አርሜናውያን ዜጎች በሀገሬ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ዜጎች ላይ እነርሱን ሊጎዱ የሚችሉ የተለያዩ የአያያዝ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋልን?…“ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ በሁሉም ዓይነት ዕድሎች ላይ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ልናስወጣቸው እንችል ነበር፣ ሆኖም ግን በፍጹም አናደርገውም፡፡ እነዚህ ዜጎች በእኛ ሀገር እንግዶቻችን ናቸው…ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢሰጡ በአንድ ጆሯችን ሰምተን በሌላው ጆሯችን እናስወጣለን…ለቱርክ ሬፐብሊክ እንደዚህ ያለ ኃጢያትን እና ወንጀልን የያዘ ነገር አንፈጽምም›፡፡

የኢርዶጋን ሊታመኑ የማይችሉ ድፍረት የተሞላበት የተዛባ ኢአመክንዮአዊ ድርጊት በቸልታ የሚታይ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢርዶጋን እ.ኤ.አ በ2015 በአርሜኒያ ዜጎች ላይ ከሀገር የማባረር እና የዘር ማጥፋት ፍጅት ያልፈጸምን መሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነ እደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ በ1915 በአርሜናውያን ህዝቦች ላይ ምንም ዓይነት የዘር ማጠፋት ድርገት ላለመፈጸማችን እንደማስረጅ ይቆጠራል የሚል ዓይነት የማሳመኛ ጭብጥ በማቅረብ ሲውተረተሩ ይታያል! በእርግጥ እ.ኤአ በ1915 በሀገራቸው ቱርክ ይኖሩ የነበሩት 2 ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ የነበሩ የአርሜኒያ ህዝቦች በምን ዓይነት መንገድ እንደዚህ ተቀንሰው እ.ኤ.አ በ2015 100,000 እንግዳ ህዝቦች በሀገራቸው ላይ እንዳሉ ግልጽ ሊያደርጉልን አልሞከሩም፡፡

በአማራጩ ደግሞ የቱርክ መንግስት በአርሜናውያን ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ፍጅት የፈጸመ መሆኑን የሚናገሩትን ሰዎች ስም ጥላሸት በመቀባት እና በመዘለፍ ምንም ዓይነት የዘር ማጥፋት ፍጅት እንዳልተፈጸመ ማረጋገጫ ሊይደርግ ይሞክራል! ሆኖም ግን ፖፕ ፍራንሲስ አካፋን አካፋ በማለት 2ኛው የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 ፖፕ ጆን ፓውል 2ኛ በተመሳሳይ መልኩ በተረጋጋ መልኩ “የዘ-ቃል/G-word“ ሳይጠቀሙ እንዲህ ብለው ነበር፣ “የሮማ ካቶሊኮች በአርሜናውያን ህዝቦች ላይ ተደርጎ በነበረው አጠቃላይ የማጥፋት ድርጊት የኃይል እርምጃ ምክንያት በጣም አስደንጋጭ ሀዘን ተጋልጠው ነበር፡፡“ ፓፓው በጸሎታቸው እንዲህ የሚል ተማጽዕኖ አቅርበው ነበር፣ “አዳምጡኝ፣ ኦ ጌታዬ  ከዚሀ ቦታ ለተነሳው ሀዘን፣ ከጥልቁ መቃብር ጥሪ ለተደረገለት ሙት፣ እንደ አቤል ደም የሌሎች ንጹሀን ሰዎች ለቅሶ፣ ምንም ባለማድረጋቸው ምክንያት ራሄል ለልጆቿ እንዳለቀሰችው ሁሉ አይተህ ምህረቱን አውርድልኝ፡፡“

የአርሜኒያውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት በዓለም የኃይማኖት መሪዎች እና በፖለቲከኞች ብቻ እውቅና የሚያገኝ አይደለም ሆኖም ግን ያ እኩይ እና ዘግናኝ ድርጊት በታዋቂ ዓለም አቀፍ ምሁራን፣ በምርምር ሰዎች እና በታሪክ ምሁራን ጭምር እንጅ፡፡ እ.ኤ.አ በ1997 የዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ፍጅት ምሁራን ማህበር (አዘማፍምማ)/International Association of Genocide Scholars (IAGS) በኦቶማን እልቂት የተፈጸመባቸውን አርሜናውያን በአንድ ድምጽ የዘር ማጥፋት ፍጅት በማለት ዕውቅና የሰጠ መሆኑን በአንድ ድምጽ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ አዘማፍምማ እ.ኤ.አ በ1915 በቱርክ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ አርሜናውያን ላይ ለተፈጸመው የጅምላ እልቂት የተባበሩት መንግስታት የዘር ማጥፋት መከላከል እና ቅጣት/United Nations Convention on the Prevention and Punishment of Genocide የተስማማበትን የጅምላ ዕልቂት አረጋግቷል፡፡ 

ቱርክ ብዙ ተቃውሞዎችን ታቀርባለች፣ በአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ጉዳዮች ላይ ያለኝ አስተያየት፣

ሸክስፒር  በአንዲት መንደር ውስጥ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ጽፈዋል፣ “ወይዘሮዋ በርካታ ነገሮችን ትቃወማለች፣ ለእኔ እንዲህ ይመስለኛል፡፡“ በአርሚኒያን ላይ ምንም ዓይነት የዘር ማጥፋት ፍጅት እንዳልተፈጸመ እና በዘር ማጥፋት ፍጅቱ ጉዳይ ላይ በምትሰጠው አመክኖያዊነት የሌለው ተከላካይነት የቱርክ መቋጫ የሌለው እና ኃይለኛ ተቃውሞ በተቃራኒው ለዓለም  ህዝብ የዘር ማጥፋት ፍጅት የተፈጸመ መሆኑን ያመላክታል፡፡  ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “ኦ፣ ሌላ ስም ቢሰጠውም ጽጌረዳ እያልን የምንጠራው አበባ በሌላ ስም ቢጠራም ያው ጥሩ ጥሩ መሽተቱን አይለውጥም፣ በስሙ ውስጥ ምን አለ?“ ሆኖም ግን የዘር ማጥፋት ፍጅት በሌላ በማናቸውም ስም ቢጠራ ያው በከፍተኛ ደረጃ መጠንባቱን አይተውም!

እውነት ለመናገር የዘር ማጥፋት ፍጅቱን የካደችው ቱርክ ብቻ አይደለችም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ፍጅት በመካዷ ከፍተኛ ለሆነ የሞራል ዝቅጠት ኪሳራ ተዳርጋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 የክሊንተን አስተዳደር በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ፍጅት ሆን ብሎ ጆሮዳባ ልበስ ብሎ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፕሬዚዳንት ኦባማ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ሱሳን ራይስ በሩዋንዳ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት እልቂት ቸልተኛ በመሆን ለድርጊቱ መፈጸም እውቅና ባለመስጠት እና ተገቢ የሆነ እርምጃ ባለመውሰድ ይከራከሩ ነበር ምክንያቱም ለእርሳቸው ለምክር ቤታዊ ምርጫ በእራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ አሉታዊ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድር ስለነበር ነው፡፡ ራይስ በበከተ የሞራል ስብዕና እና በምን አገባኝነት መንፈስ በመሞላት አንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥው ነበር፣ “ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል የምንጠቀም ከሆነ እና ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ በሩዋንዳ ምንም ነገር ማድረግ የማንችል ከሆነ በህዳር በሚደረገው የምክርቤታዊ ምርጫ ምን ዓይነት ውጤት ሊከተል ይችላል?“ (በክሊንተን አስተዳደር ክህደት የተፈጸመበትን የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት እልቂት ያዘጋጀሁትን ሙሉ ትችት እዚህ ጋ በመጫን ያንብቡ፡፡)

የሩዋንዳን ህዝብ የመጭፍጨፉ ድርጊት እ.ኤ.አ ሚያዝያ 7/1994 ተጀምሮ እስከ ሀምሌ ድረስ ቀጠለ፡፡ ሚያዝያ 23 የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ዋና ዓርታኢ እንዲህ የሚል መግለጫ አወጣ፣ “በሩዋንዳ የሚካሄደውን የዘር ማጥፋት ፍጅት የመሰለ አስቀያሚ ነገር ምን አለ? ህዝቦች ከመኪኖች እና ከአውቶብሶች እየተጎተቱ እንዲወርዱ እየተደረገ የማንነት መለያ ወረቀቶቻቸውን እንዲያሳዩ እየታዘዙ የሌላ ጎሳ አባል መሆናቸው ከተረጋገጠ ወዲያውኑ በዚያው ቦታ ላይ ይገደሉ ነበር፡፡   “

በሺዎች የሚቆጠሩ ሬሳዎች በአንድ ላይ እንደበረዶ ቁልል ተከመሩ፡፡ እናም 1700 የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዚያች ሀገር የነበሩ ቢሆንም ቅሉ ግድያው በተጠናከረ መልኩ ቀጠለ፡፡ ፕሬዚዳንት ክሊንተን በኋላ ላይ እንዲህ በማለት አዘኑ፣ “ቀደም ብለን ብንደርስላቸው ኖሮ በዚያ ዕልቂት ከሞቱት ቢያንስ የአንድ ሶስተኛውን ህዝብ ህይወት ማትረፍ እንችል ነበር…በእኔ ላይ የሚያስጨንቅ ስሜትን ፈጥሯል፡፡“ ከዚያ የዘር ማጥፋት ድርጊት ቢያንስ 300,000ን ከእልቂት ማትረፍ እንችል ነበር! 

እውነት እና ዕርቅ፡ ከአርሜኒያ የዘር ማጥፋት እልቂት ትምህርት መውሰድ እና ዓለም አቀፍ በጥፋተኝነት ያለመጠየቅ እና የዘር ማጥፋት ባህልን ማቆም፣ 

የአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ፍጅት ለበርካታ አርሜናውያን የማይድን የአዕምሮ ቁስል ሆኗል፡፡ ያ አስከፊ የነበረው የዘር ማጥፋት ፍጅት ትውስታ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በመሸጋገር ላይ ይገኛል፡፡ ለ100 ዓመታት ያህል ተክዶ እና ጸጥ ተብሎ የቆዬውን ያንን አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ፍጅት የማቆሚያ ጊዜው አሁን ነው፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ለዓለም ህዝብ ያስተማሩት ታላቅ ትምህርት የዕውነት እና እርቅን ከፍተኛ ጠቃሚነት ነበር፡፡ ቱርኮች ይፋ በሆነ መልኩ በአርመናውያን ላይ የፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀል አምነው እስካልተቀበሉ ድረስ በአርመን እና በቱርክ ህዝቦች መካከል ትርጉም ያለው ዕርቅ ሊኖር አይችልም፡፡ እውነት ብቻ በአርሜናውያን ትውልድ የመረቀዘውን የትውልድ ነብስ የህሊናን ቁስል ያድናል፡፡

ማንዴላ በአፓርታይድ የጥላቻ እና የዘረኝነት ስርዓት የቆሰለውን ቁስል በማስተማር እና ይቅርታ በማድረግ የህሊናን ቁስል መፈወስ እንደሚቻላል አሰተምረዋል፡፡ ይቅርታ የማድረግ ሂደት በመጀመሪያ ደረጃ የዕኩይ ድርጊት አራማጆች በዜጎች ላይ የፈጸሟቸውን እልቂቶች ተገንዝበው ያለምንም ማመንታት እውቅና መስጠት እንዳለባቸው እምነት አለኝ፡፡

ማንዴላ የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ዘገባን በተቀበሉበት ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዛሬ ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ ረኃብ መጨረሻ የዘራናቸውን ጥቂት ምርቶች በመሰብሰብ ላይ እንገኛለን፡፡ እናም ይህንን አዝመራ በበዓሉ አከባበር ላይ እና በሀዘናችን ላይ ሆነው በመከታተል ህይወታችንን ለማስቀጠል፣ እንደማህበረሰብ ህልውናን ለማስጠበቅ እና የእኛ ትውልድ እንዲያውቁት ለማድረግ እንዲሁም በመጨረሻ ወደማይቀረው ዓለም ለዘላለም እስከምንሄድ ድረስ ለእኛ ህልውና ቀጣይነት እንደገና መዝራት እንዳለብን፣ በተደጋጋሚ እና በቀጣይነት መዝራት እንዳለብን መገንዘብ እና ሁለቱን ቀላል ቃላት ማለትም “እንደገና በፍጹም” የሚሉትቃላት ተግተባራዊ እስከሚሆኑ ድረስ የማምረት ትግሉ ይቀጥላል!“

የዕውነት እና የዕርቅ ሌላው ተቃራኒው ነገር ደግሞ የታሪክ እስረኛ መሆን እና የበለጠ የዘር ማጥፋት ፍጅት በመፈጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥፋተኝነት ተጠያቂ ያለመሆን እና ክህደት እንዲፈጸም ማድረግ የሚለው ነው፡፡

የዘር ማጥፋት ፍጅትን ያለመቀበል እና መካድ ለሌላ የዘር ማጥፋት ፍጅት ግብዣ የመጥራት ያህል ነው፡፡ ቱርክ በአርሜናውያን ላይ የፈጸመችውን የዘር ማጥፋት ፍጅት ምንም ሳትሆን ማድረግ እንደምትችል የሚፈቀድላት ከሆነ ሌላ ማንኛውም ሀገር ተመሳሳዩን ነገር ይፈጽማል፡፡ በእርግጥ ያ ዕልቂት ያለማንም ተቀናቃኝነት ተፈጽሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 ኦማር አልባሽር ከቱርክ እልቂት ትምህርት በመውሰድ የእርሱ መንግስት ምንም ዓይነት የዘር ማጥፋት ፍጅት ወይም ደግሞ ዘር መፍጀትን ያለምንም ስጋት በዳርፉር ላይ ፈጸመ፡፡ ባሽር በዳርፉር ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ፍጅት እንዳልተፈጸመ ሲናገር እና የዩናይት ስቴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓውልም ተራ ፈጠራ ነው ብለው የባሽርን ክህደት አጣጥለውታል፡፡

ባሽር ዩኤስ አሜሪካ ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል በመውሰድ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ለማሳካት ነው የጠቀሙበት ብለዋል፡፡ እነርሱም፡ 1ኛ) የዳርፉርን የተፈጥሮ ዘይት እና ጋዝ በመቆጣር ለእራሳቸው ጥቅም ለማዋል እና 2ኛ) ዳርፉርን ከሱዳን ነጥሎ ለማስወጣት ነበር፡፡

በሰሩት ጥፋት ያለመጠየቅ እና ክህደት የመፈጸም ባህል መቆም አለበት፡፡ ቱርኮች እና የዓለም ህዝብ በአርሜናውያን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማፋት ድርጊት ማመን እና እውቅና መስጠት አለባቸው፡፡

የአርሜናውያን የዘር ማጥፋት ፍጅት እውነታ ቱርኮችን ነጻ ሊያወጣቸው ይችላል፣ እናም የአርመናውያንን ቁስል ይሽራል፡፡

በመጨረሻው ጊዜ ወደማይቀረው ዓለም ሄደን ስናርፍ የእኛ ልጆች እውቀትን በመያዝ እንዲህ በሚሉት ቀላል ቃላት ይገዛሉ፡ እንደገና ፍጹም!

ኔልሰን ማንዴላ

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሚያዝያ 15 ቀን 2007 .