ስለ ኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡ ከፍል 1- 3

Print Friendly, PDF & Email

ስለ ኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡ ከፍል 1

(በይታያል የሩቅሰው)

ስለ ኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡ ከፍል 1- 3 pdf

መነሻዬ ሰመረ ዓለሙ የተባሉ ሰው፡ ካቀረቡት ጽሁፍ መካከል፡ አንዱን በማንበቤ ስለተጠቃሹ ከማውቀው እውነት ጥቂት ቆንጥሬ በሚከተሉት አርዕስቶች በመክፈል፡ የነጠረውን ሀቅ እያነሳሁ አንድ ሁለት ለማለት ነው።

ስለዚህ

1. ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ምን ሰርቶ ነበር?

2. የመሰወሩ ምክናያቶችስ ምንና እነማን ናቸው?

3. እኛስ ስለ እሱ ምን ብለናል?

4. ወደፊትስ ምን ማለት አለብን?

የሚሉ ሃሳብና ጥያቄዎችን እያነሳሁ ባጭሩ ለመዳስ ልሞክር።

ለዛሬ

1.1. ኮሎኔል ታደሰ ምን ሰርቶ ነበር፡

Colonel-Tadesse-Muluneh

ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ

ገና በለጋ እድሜው ዝነኛውን፡ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የተቀላቀለው፡ ታደሰ ሙሉነህ በኮሌጁ የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቅቆ፡ በምክትል፡ መቶ አለቅነት ማህረግ እንደተመረቀ ነበር፡ በሲያድባሪ የሚመራው የሶማሌ ተስፋፊ ጦር ኢትዮጵያን የወረረው፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው፡ ወቅቱ የሃይለስላሴ መንግስት፡ ወድቆ ደርግ ስልጣን የያዘበት ስለነበር ሀገራችን ለመከላከል የምታደርገውን እንቅስቃሴ፡ የሚደግፍላት ባልነበረበት ሁኔታላይ ስትሆን፡ ባንጻሩ ሶማልያ የረጅም ጊዜ የወረራ ዝግጅት ከማድረጓም በላይ ሶቬት እስካፍንጫዋ ያስታጠቀቻት በመሆኑ፡ በሁሉም ዘርፍ የእኛና የጠላት ሐይል አሰላልፍ፡ የሰማይና የመሪት ያክል፡የተራራቀ ነበር ማለት ያስደፈራል።

ደርግ በአንድ በኩል ከምዕራባውያን መንግስታት መሳሪያ ለማግኘት፡ በሌላበኩል ወታደር መልምሎ በማሰልጠን ለውጊያ ዝግጁ ለማድረግ፡ በሚሯሯጥበት ወቅት፡ የሶማሌ ታንክና ልዩ ልዩ ከባድ መሳሪያዎችን፡ የጫኑ በሺ የሚቆጠሩ፡ ተሽከርካሪዎች ባይድዋ መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ይደርሰዋል፡፡ ይህ ሃይል ወንዙን ከተሻገረ፡ ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ከመግባት የሚያግደው፡ ነገር እንደማይኖር ሰለሚገመት፡ ምንም እነኳን በተጠናከረ የአየር መቃወሚያና፡ እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች የሚጠበቅ ቢሆንም፡ የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ያ እንደጉንዳን የሚርመሰመስ ታንክና ከባድ መሳሪያ የጫነ መኪና ሳይሻገር፡ ድልድዩ መፍረስና ተመልሶ እስኪሰራ፡ ጥቂትም ቢሆን የዝግጅት ጊዜ መገኘት እንዳለበት፡ በባለ ስልጣናቱ ስለታመነ ለአየር ሃይላችን የውጊያ ትህዛዝ በመሰጠቱ፡ ግዳጁ ለም/ መቶ አለቃ ታደሰ ሙሉነህና ለበዛብህ ጴጥሮስ፡ በመሰጠቱ ወደ ቦታው ይከንፋሉ፡፡ በተጠንቀቅ ይጠባበቅ የነበረው የሶማሌ ወራሪም ገና በርቀት አየር መቃዎሚያውን ቢያስወነጭፍም፡ 2ቱ ጀግኖችና እውነተኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፡ በድፍረት ገስግሰው ተፈላጊውን ኢላማ መትተው ድልደዩን በማፍረስ፡ ፊታቸውን ወደ ሃገራቸው ሲያዞሩ ታደሰ ያበረው የነበረው ተዋጊ አውሮፕላን፡ በሶማሌ አየር መቃወሚያ በመመታቱ መንደድ ሲጀምር ወጣቱ ፓይለት በፓራሱት በመውረድ፡ በጉዞ ላየም ብዙ አስደናቂ ታሪኮችን እያከናወነ በጣም አስቸጋሪ ጉዞ በማድረግ፡ ኦጋዴን የሚገኜውን የወገን ጦር በመቀላቀሉ፡ የኢትዮጵያ ጀግና መዳሊያ የተሸለመ ከመሆኑም በላይ፡ ከም/ መቶ አለቅነት አንድ ደረጃ በመዝለል የሻበልነት ማህረግ የተሰጠው፡ ጀግና ነው።

ኮሌኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ከዚያም በሗላ በርካታ ሃገራዊ ግዳጆችን የተወጣና ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ያከናወነ፣ በትምህርት ዝግጅቱም የ2ኛ ዲግሪውን በማዕረግ ያጠናቀቀ፡ ፍጹም ሐገር ወዳድ፣ ቅንና እሩህ ሩህ፣ አርቆ አስተዋይ፡ ባጠቃላይ እንከን የለሽ ስብናን የተጎናጸፈ፡ ሲሆን ወያኔ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር፡ የጠላትን ፊት ላለማየት፡ ከድሪድዋ አውሮፕላን አስነስተው፡ ኬንያ ከገቡት የአየር ሃይል አብራሪዎቻችን አንዱ ነበር።

ከዚያም የሀገሩ ውድቀት የእግር እሳት የሆነበት፡ ኮሎኔል ታደሰ ኬንያ እየኖረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፡ ለማካሄድ ሲጀምር ሁኔታዎች ለህይወቱ አድገኛ ሆነው ስላገኛቸው፡ የተሻለ ከለላ ለማግኘት ባደረገው ጥረት የዑጋንዳ ባለስልጣናትን አነጋግሮ ባገኜው ይሁንታ መሰረት ወደዚያው ሄዶ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንዳለ፡ የወያኔና የሻብያ ግንኙነት፡ በመበላሽት ላይ እንደሆነና፡ ሻብያ ወያኔን በጦር ሃይል ለማንበርከክ፡ ሚስጥራዊ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ፡ በአንድ የድሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባና ኤርትራ ከተገነጠለች በሗላ የኤርትራ ባለስልጣን በሆነ ግለሰብ፡ ይነግረውና፡ ኢትዮጵያን ከወያኔ ነጻ የማውጣት እቅዱን በኤርትራ በኩል ቢያደርግ እንደሚሻል ያግባባዋል፡፡

ኮሎኔል ታደሰም፡ የጠላቴ ጠላት የእኔ ወዳጄ ነው ወይንም ጅብን ለመውጋት አህያን መጠጋት እንዲሉ፡ ከስልት አንጻር ከዚህ የተሻለ ቦታ የለም በማለት፡ ጥያቄውን ተቀብሎ ወደ ኤርትራ በማምራት የሃገሪቱን መሪ በአካል አግኝቶ ሲያነጋግር፡ ሁኔታወች እስኪመቻቹልህ ድረስ፡ የኤርትራ ተዋጊ ጀት አብራሪዎችን ሲያሰለጥን እንዲቆይ፡ ትብብር ስለተጠየቀ እሽ ብሎ እያሰለጠነ ለሁለት አመት ያህል እንደቆዬ፡ ወያኔ ሳያስበው፣ ሻብያ ግን ከ3 አመት ባለነሰ ዝግጅት ጦርነቱ በሻብያ ተንኳሽነት ይፈነዳል።

ይህነን ተከትሎ ደግሞ በኬንያም፣ በሱዳንም፣ በሃገር ቤትም፡ ይንቀሳቀሱ የነበሩ፡ የወያኔ ተቃዋሚዎች ኤርትራ ገብተው፡ ከእዚያ እየተንደረደሩ ወያኔን መውጋት ይችሉ ዘንድ፡ ለኤርትራ መንግስት ጠያቄ አቅርበው ስለተፈቀደላቸው፡ ጠቅልለው እንደገቡ ከኦነግና ከኦቭነግ በቀር፡ ሌሎቹ ግንባር ፈጥረው በአንድ ድርጅት ጥላ ስር በመሰባሰብ ለውጊያ እንዲዘጋጁ፡ በሻብያ መመሪያ ስለተሰጣቸው፣

1ኛ. በአቶ ዮሴፍ ያዘው፡ ይመራ የነበረው፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራ ግንባር፡

2ኛ. በአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ይመራ የነበረው፡ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ንቅናቄ፡

3ኛ. በአቶ ቱሗት ፖል ይመራ የነበረው፡ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር፡

4ኛ. በአቶ ጁማ እሩፋኤል ይመራ የነበረው፡ የቤንሻንጉል ንቅናቄ፡ በጋራ ባደረጉት የውህደት ጉባኤ ላይ ኮሉኔል ታደሰ ሙሉነህም

ተካፋይ እንዲሆን ትደርጎ ስለነበር፡ ተዋህደው አዲሱን ድርጅት የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የሚል ስያሜ በመስጠት የመጀመሪያ ጉባያቸውን ሲያጠናቅቁ፡

1ኛ. ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህን፡ የግንባሩ ሊቀመንበር፡

2ኛ. አቶ ቱሗት ፖልን፡ የግንባሩ ም/ሊቀመንበረ፡

3ኛ. አቶ ጁማ እሩፋኤልን የግንባሩ ጽሃፊ፡

4ኛ. አቶ ዮሴፍ ያዘውን የግንባሩ ድርጅት ጉዳይ፡

5ኛ. አቶ ተሰፋዬ ጌታቸውን የግንባሩ የእርዕዮታለም ጉዳይና ሌሎች 2 ሰወችን በማከል፡ 7 ያመራር አካላትን መርጠው ነበር።

ኮሎኔል ታደሰ ያካበተውን የጠለቀ እውቀትና ሰፊ የስራ ልም፡ ሳይሰስት ተግባር ላይ ስላዋለው፡ አርበኛ ግንባር ባጭር ጊዜ በብዛትም ሆነ በጥራት ጠላቱን ወያኔን ብቻ ሳይሆን፡ አስተናጋጇን የኤርትራን መንግስትም፡ ከማስፈራት ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ፡ በዲፕሎማሲውም ዘርፍ ኮሎነል ታደሰ ወደ አውሮፓና አሜሪካን በመጓዝ፡ ኢትዮጵያውያንን አነጋግሮ በማሳመን ሰፊ ድጋፍን ያስገኘ ሰው ነው።

ኮሎኔል ታደሰ ወደ አሜሪካን ባቀናበት ወቅት፡ ሻብያን በጥርጣሪ አይን የሚያዩ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ተሰባስበው መኝታ ክፍሉ ድረስ በመሄድ፡ በሻብያ ድጋፍ ኢትዮጵያ ነጻ ትወጣለች ብለህ አትድከም ይልቅ፡ ሻብያ እንደበግ አስብቶ ሳያርድህ፡ አሁን እንደወጣህ በእዚሁ ቅርና ልጆችህን አሳድግ፣ ሚስትህም፡ ኢትዮጵያም ያንተ ብቻ አይደለችም፡ ወ.ዘ.ተ. በማለት ቢለምኑት፡ የሰጣቸው መልስ፡ ሁሉም ኢዮትጵያ ለእኔ ብቻ አይደለችም፡ እያለ ጥሏት ከሸሸ የጎርቤት ሀገር ዜጋ መጥቶ ሊታደጋት ነውን? ባለቤቴም ሆኑ ልጆቸ አሜሪካን ገብተዋል፡ የተሻለ ኑሮ እየኖሩ ነው ወደፊትም ቢሆን እኔ ኖረሁም አልኖርሁም ይኖራሉ፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ግን ይህንን እድል ማግኘት አይደለም በሀገሩ ላይ በሰላም የመኖር መብቱ ተገፍፎ 2ኛ ዜጋ ሆኖ በመማቀቅ ላይ ከመሆኑም በቀር፡፡ ወያኔ ውሎ ካደረ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር አትኖርም፡ እናም ቢሆን ከጥፋት አድናታለሁ፡፡ ካልሆነም ጥፋቷን ሳላይ ማንም ያጥፋኝ ማን ስከላከልላት እኔ ቀድሜያት፡ እጠፋለሁ፡፡ ሞት እንደሁ ፈራንም ደፈርንም፡ የማይቀር የተፈጥሮ እዳችን ነው። የሚል እንደነበር ካነጋገሩት ሰዎች መካከል አንዱ ሰሞኑን በቁጭት አጫውተውኛል።

ለዛሪ በዚህ ላብቃ ቀሪውን በክፍል ሁለት ሳምንት እመለስበታለሁ፡

የሳምንት ሰው ይበለን፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይታደጋት አሜን!!!!

 

 

ሰለኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡ ከፍል 2

ይታያል የሩቅሰው

ወደ እለቱ ተግባራዊ ቅኝቴ ለመግባት፡ ባለፈው ሳምንት በዚህ አርእዕስት የከተብሗትን፡ ጦማሪን ስደመድም፡ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ወደ አሜሪካን ባቀናበት ወቅት፡ በዚያው እንዲቀር ለቀረበለት ጥያቄ፡ የሰጠው መልስ፡ወያኔ ውሎ ካደረ ኢትዮጵያ የምትባል ሃአገር አትኖርም፡ እናም ቢሆን ከጥፋት አድናታለሁ፡ ካልሆነም ጥፋቷን ሳላይ ማንም ያጥፋኝ ማን ስከላከልላት እኔ ቀድሜያት፡ እጠፋለሁ፡ ሞት እንደሁ ፈራንም ደፈርን፡ የማይቀር የተፈጥሮ እዳችን ነው። የሚል እንደነበር በመጥቀስ ነበር፡፡ ወደዛሪው የምገባው ደግሞ የሚከተለውን ጥያቄ ለመመለስ በመሞከር ነው።

2.1. የመሰወሩ ምክናያቶችስ ምንና እነማን ናቸው?

ነገሩ እንዲህ ነው፣ በኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ የሰከነና፡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር፡ በእነ ቱሗት፣ በእነ ጁማ፣ በእነ ዮሴፍ፣ በእነተ ስፋዬ፡ ትጋትና የዓላማ ጽናት፡ ያልተለየው የሌት ከቀን እንቅስቃሴ፡ በክፍል አንድ ማብራሪያዬ፡ እንደጠቀስሁት፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፡ በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ፡ ጥቃት መሰንዘር ከሚያስችለው ደረጃ ላይ እየደረሰ ሲመጣ፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ በርካታ፡ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፡ እቦታው ድረስ በመሄድ ጎብኝተው፡ ትግሉን በማበረታታት ወደ እየመጡበት ሲመለሱ፡ ፕ/ር ሙሴ ተገኝ ግን፡ ጓዙን ጠቅልሎ አስመራ በመግባት፡ አይዟችሁ በማለት ፋንታ፡ ከተማ ቁጭ ብሎ፡ የግንባሩ መሪ ለመሆን ባለው ህልም፡ ይሁን በሌላ ልዩ ተልዕኮ፡ ባለየለት ምክናያት፡ በኤርትራ ባለስልጣናት ቢሮዎች እየዞረ፡ እነ ኮሎኔል ታደሰን፡ እነዚህን ደርጎች፡ እንዴት ታምኗቸውአላችሁ፡ በማለት ማጥላላትን ስራየ ብሎ ይይዛል፡ አመራሩ ግን፡ ከሗላው እየተለቀለቀበት ያለውን ጥላሽት፡ በማያውቅበት ሁኔታ ላይ ሆኖ፡ ብዙ ኩነቶችን ከዳሰሰና፡ ካጠና በሗላ የውጊያ እቅድ ሲነድፍ፡ አንድ መደምደሚያላይ ይደርሳል። እሱም የትግሉ መሰረት የጎረቤት ሀገር ሳይሆን ሃገር ቤት መሆን አለበት። የወደቀው ወድቆና ያለቀው አልቆ፡ ሀገራችን ላይ ነጻመሪት ሊኖረን ይገባል፡ የሚለው ተወስኖ ጠቅልሎ ለመግባት የ6ወር ጊዜ ገደብ ተቀምጦለት፡ ዝግጅት ይጀመራል፡ ጉዳዩም በሚስጥር እንዲያዝና ከስራ አመራሩ በቀር ለማንም እንዳይወራ፡ ተስማምተው በእየተመደቡበት የስራ ዘርፍ ደፋቀና በማለት ላይ እንዳሉ፡ ከ7ቱ አመራር አባለት መካከል አንዱና በገንዘብ ያዥነት፡ የተመደበው አበሩ አታላይ ማለት ዛሪ ስሙን ቀይሮ መስከረም ነኝ ያለውና፡ ጀርመን ሃገር የሚኖረው፡ ለህክምና ብሎ አስመራ በሄደበት ከፕ/ር ሙሴ ተገኝ ጋር ተገናኘቶ 2ቱ የተንኮል ሴራ ሽርበው፡ በጋራ ከአንድ የሻብያ ቱባ ባለስልጣን ቢሮ ቀጠሮ አስይዘው በመግባት፡ እነዚህ ደርጎች እነ ኮሎኔል ታደሰን ማለት ነው፡ ጓዛቸውን ጠቅልለው ሀገራቸው ሊገቡ ወስነው እየተዘጋጁ ነው ያሉት፡ እንዲያውም፡ በመጀሪያ፡ ወያኔን ቀጥለን ሻብያን፡ እንደመስሳለን፡ ሀገራችን ወደብ አልባ ሆና አትቀርም ነው የሚሉት፡ በማለትና ሌሎች ሻብያን ሊያበሳጭ ይችላል ያሉትን ውሽት በመደርደር፡ መረጃ ሰጥተውና ለቀጣይ መመሪያ ተቀብለው ይወጣሉ። ከዚያች እለት ጀምሮ እነ ኮሎኔል ታደሰ በሻብያ አይነ ቁራኛ መጠበቅ ይጀምራሉ፡፡ አበሩ አታላይም ወደግንባር ተመልሶ፡ የጎንደር አካባቢ ተወላጅ ሲያገኝ፡ ጎነደሬ፡ የትግራይ ካባቢ ተወላጅ ሲያገኝ፡ ትግሬ ነኝ በማለት፡አቅሙ በፈቀደ መጠን ሰራዊቱን፡ በመንደር መከፋፈሉን ያጧጡፋል።

ነገር ከስሩ ውሃ ከጥሩ እንዲሉ፡ ለአነባብያን፡ የበለጠ ግልጽ እንዲሆን፡ ትንሽ ወደሗላ ሄጄ፡ ሰለ አበሩ አታላይ፡ ማንነት በአጭሩ፡ አንድ ሁለት ልበል፡ ተጠቃሹ፡ ወልቃይት ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው፡ ትምህርት፣ የሚሉት ነገር ባህላዊዩም ሆነ ዘመናዊዩ አልነኩትም በፍጹም አይተዋወቁም፡ በማህበራዊ ኑሮውም በአካባቢው የተጠላ ነበር፡ ያነን ማንነቱን የፋቀልኝ መስሎት ሳይሆን አይቀርም ስሙን መቀየር ያስፈለገው። ይህ ግለሰብ የሚኖርባት መንደር የጎንደር ክፍለሀገር ክልል ሆና፡ የትግራይንና የኤርትራን ክፍላት ሀገራት በቅርብ እርቀት የምታዋስን በመሆኗ፡ በደርግ ዘመን፡ በሚፈጽማቸው አስነዋሪ ተግባራት፡ ምክናያት በፖሊስ፡ ጎንደር ሲፈለግ ትግራይ፣ ትግራይ ሲፈለግ ኤርትራ፡ እያለ በማስቸገር ሲኖር፡ በአንድ ወቅት ብልሁ የሀገሪ ሰው በዘዴ ለመገላገል፡ሲል ለአካባቢ ህዝባዊ ሰራዊትነት መልምሎ እንዲሰለጥን

ይልከዋል፡ አበሩ ከተላከበት ጠፍቶ ወደመንደሩ ሲገሰግስ አዘዞ ላይ ተይዞ፡ በሀገር ክህዕደት ወንጀል ተፈርዶበት እስር ቤት ይገባል፡ ጨርሶ ሲወጣ፡ ወደመንደሩ ሄዶ የተለመደ ስራውን ሲያከናውን፡ ወያኔ ሀገሪቷን ይቆጣጠራል፡ ወያኔዎች እንደገቡ ሌባ ይገድሉ ስለነበር እንዳይገደል ፈርቶ፡ ወደሱዳን ይሸሻል፡ እዚያም ከፋኝን ተቀላቅሎ፡ እያለ የከፋኝ መስራችና ነባር አባላቱም ሆኑ መሪዎቹ በዩ.ኤ.ን. አማካኝነት፡ ወደተለያዩ ምእዕራባውያን ሀገራት ሲሄዱ፡ እሱ በመቀረቱ፡ በአቶ ዮሴፍ ያዘው የሚመራውን፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሴያዊ ግንባርን፡ተቀላቅሎ ኤርትራ ይገባና፡ የትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪነቱን፡ እንደ ማንነት መገለጫ በማቅረብ፡ በድብቅ በአካባቢው፡ ላገኛቸው የኤርትራ ባለስልጣናት ኤርትራዊ እነቱን በመንገር፡ የሻብያ አባል ይሆንና፡ አብረውት የተሰደዱ ኢትዮጵያንን፡ እንዲሰልል ግዳጅ ተሰጥቶት እያለ ነው ተጨማሪ ሐይል ሙሴ ተገኝን ያገኘ።

ስለ መስከረም አታላይ፡ ከብዙው በጥቂቱ፡ ይህነን ያህል ካልሁ ወደ ኮሎኔል ታደሰ ልመለስ፡ እነኮሎኔል ታደሰ ባላወቁት ነገር በሻብያ ጥርስ ተነክሰው፡ የሚደነቀርባቸውን ሁሉ መሰናክል በትግስት እያለፉ፡ ስራቸውን በማፋጠን ላይ እንዳሉ፡ ከእለታት አንድ ቀን በሻብያ ሰራዊት ተከብበው፡ አመራሩ እንዲበተን ይደረጋል፡ ከዚህ በሗላ ኮሎኔል ታደሰ፡ ከአስመራ እንዳይወጣ ሲደረግ ቱሗት ፖልና ጁማ እሩፋኤል፡ ከኤርትራ እንዲወጡ፡ ዮሴፍ ያዘው ከተሰኔይ ከተማ እንዳይወጣ፡ ሲደረግ ተስፋዬ ጌታቸው፡ አዚያው ሃሪና በርሀውስጥ እንዲታሰር ተወሰነበት፡፡ይህ ከመከናወኑ ቀደም ብሎ ግን የግንባሩ አመራር ከነደፈው፡ መርሃግብር አንዱ የሆነውን አርበኛው፡ ከኤርትራ ነቅሎ ሲወጣ፡ መሰረቱን የሚጥልበትን ቦታ፡ አጥንቶ እንዲመለስ የተመደበውን ቃኝ ሃይል፡ በሃላፊነት መርቶ የሚሄድ አንድ ሰው ለመምረጥ፡ በተደረገ ውይይት ላይ፡ አበሩ ወይንም መስከረም አታላይ፡ በእራሱ ፈቃድ እኔ ልሂድ ስለአለ፡ በሃላፊነት መርቶ እንዲሄድ ይደረጋል፡ አበሩ ከፊሉን አስገድሎና ከፊሉን፡አስማርኮ፡ እሱ ብቻውን፡ ጥይት አይደለም እንቅፋት ሳይመታው፡ ከመመለሱም በላይ ኪሱ ውስጥ በርካታ ዶላር በመገኘቱ፡ ጉዳዩ አጠራጣሪ ሆኖ ስለተገኘ፡ እስኪጣራ አመራሩ አስሮት ከነበረበት፡ በሻብያ ትእዕዛዝ ተፈትቶ፡ አሁንም ያለምርጫ፡ በሻብያ ትእዛዝ የግንባሩ፡ አዛዥ እንዲሆን ሲመደብ፡ በአንድ በኩል የፕ/ር ሙሴ ተገኝ የመሪነት ህልምን ሲያከስም፡፡ በሌላበኩል ሰራዊቱን፡ አስቆጥቶ፡ ከመበታተን፡ ደረጃ አደረሰውና፡ የተበተነው የሰው ሐይል፡ ከፊሉ ሱዳን ሲገባ ከፊሉ ደግሞ ወደሀገሩ የተመለሰ ሲሆን፡ ሁለቱንም ማድረግ ያልቻለው፡ መሀይም አይመራንም፡ አበሩ አታላይ፡ ታደሰ ሙሉነህን ሊተካ አይችልም፡ በማለት፡ የደቡብ ህዝቦች፡ የሲዳማ ህዝቦች፣ የጋቤላ፣ የቤንሻንጉል ወ.ዘ.ተ. በሚል ተከፋፍሎ፡ እነሆ ዛሪ የምንሰማውን 8 የብሄረሰብና የቋንቋ ድርጅት አቋቁሞ፡ እዚያው ኤርትራ ውስጥ እየኖረ ይገኛል። አበሩ አታላይም፡ በጣም ጥቂትና በግንዛቤም ሆነ በአቅም የሚመሳሰሉተን፡ የመንደሩን ልጆች አሰባስቦ፡ የአርበኛ ግንባር የሚለውን ስም፡ እንደያዘ አዛዥ ነኝ በማለት፡ ተስፋዬ ጌታቸውን ጉድጓድ ውስጥ አስሮ እንደውሻ በዱላ ደብድቦ ገደለው። በዚያን ጊዜ በአበሩ አታላይ፡ የተጀመረው፡ ወያኔን የምንጠላበት፡ የመንደርተኝነት፡ አባዜ እረ ወያኔስ ቢያንስ ከፍ አድርጎ፡ በቋንቋ ነው የከፋፈለን፡ አበሩ ግን አውርዶ፡በቀበሌ ገነጣጥሎን፡ አርበኛ ግንባር ውስጥ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ እየሰራ ሲሆን፡ አመራር አይደለም፡ የአርበኛ ግንባር ታማኝ አባል ለመሆን፡ ቢሆን ወልቃይት፣ ካልሆነም ጎንደር መወለድ የግድ ይላል፡፡ ባልተጻፈው በእነ መስከረም፣ ማእዛው መመሪያና ደንብ፡ መሰረት፡፡ ለዚህም ነው አረበኛ ግንባር በተለያየ ጊዜ ከገደላቸው፡ ሁሉ ምሁራን፡ መካከል ከካሳሁን ወንዴ በቀር ጎንደር ክፍለሀገር የተወለደ፡ ሌላ2ኛ ሰው የማይገኝበት።

ከእነ ታደሰ ሙሉነህ፡ በሗላ ያለው አርበኛ ግንባር፡ ተስፋዬ ጌታቸውን ብቻ አይደለም የገደለው ወደፊት ታሪክ የሚያወጣቸው፡ ለመታገል የገቡ በመቶወች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን፡ እንክት አድርጎ በልቷል፡ ለዚህ ድርጅት አመራር አካላት ፊደል የቆጠረ ሰው፡ ከወያኔ በላይ ያስፈራቸዋል፡፡

መስከረም አታላይ፡ እሱ በሻብያ እንደተሾመ ሁሉ ከ3 አመት ቆይታ በሗላ፡ ወደጀርመን ሲጓዝ በተራው ደገሞ፡ መጻፍና ማንበብ የማይችለውን፡ የታላቅ እሀቱን ልጅ፡ ማእዛው ጌቱን፡ ሾሞት ስለሄደ 9 አመት ሙሉ አርበኛ ግንባር፡ የሚመራው በእሱ ነው፡ ያሳያችሁ እንግዴህ በተራቀቀ ሳይንስና ቴክኖለጅ፡ የሚጠቀምን ጠላት ለማስወገድ እታገላለሁ የሚል ጦር አዛዡ፡ ይህ ሰው ነው፡ ታዲያ፡ ለምን አይዳከም? ለምንስ አይክሰም? በእውቀት የበሰሉ፣ በሙያው የተካኑ፣ ኢትዮጵያውያን ሲቀላቀሉት፡ ፈጥኖ ይበላቸዋል፡ ለእነ ማዛው ስልጣን ስለሚያሰጉ። የኮሎኔል ታደሰ መሰወር መንስኤው ሌላ ምንም ሳይሆን ይኸው ነው፡ ለእነማእዛው ስልጣን እንዳያሰጋ ገለል ማለት አለበት። ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ከአስመራ እንዳይወጣ ተወስኖበት ሲኖር፡ ከዲያስፖራ አርበኛውን ለመጎብኘት የሚሄድ፡ ሁሉ ኢትዮጵያዊ የአመራሩን ደካማነት ሲያይ፡ በማዘንና ተስፋ በመቁረጥ፡ ምናለ ኮሎኔል ታደሰ አመራሩን እንዲረከባችሁ ብታደርጉ የሚል ከቅንነትና ከመቆርቆር የመነጨ፡ አስተያይት፡ ተደጋግሞ እየተሰነዘረ ስላስቸገራቸውና፡ኮሎኔል ታደሰ አመራሩን ተረክበ ማለት ደግሞ፡ በምርጫ የማይቀየረውና፡ በማእዛው፡ የሚመራው 7ቱ የስራአመራር፡ ኮሚቴ ከዲያስፖራ እየተዋጣ፡ የሚላክላቸውን ዶላር በማዘርዘር፡ ተሰነይና ጉልሽ ከተሞች ላስቀመጧቸው የኤርትራ ቆነጃጅት፡ አልባሳትና ከእግር ጥፍራቸው እስከ እራስ ጸጉራቸው፡ የሚንቀለቀሉበት ወርቅ፡ መግዛቱ የሚቆም ከመሆኑም በላይ፡ ያመራር ቦታው፡ ወልቃይት በመወለድ ሳይሆን፡ በብቃት በሹመት ሳይሆን በሰራዊቱ የተመረጡ ሰዎች የሚይዙት ስለሆነ፡ ከአዛዥነት ወደታዛዥነት ሊወርዱ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ዘላቂ መፍትሄና፡ ስጋትን አስወጋጅ ነው ብለው ያሰቡት፡ ኮሎኔል ታደሰን፡ ወንጅሎ ቢሆን ተላልፎ ለእነሱ ተሰጥቷቸው፡ እንደተስፋዬ ጌታቸው፣ እንደ ካሳሁን ወንዴ እንደ ጌታቸው ብርሃኑ እንደ ወርቅነህ መበሩ፡ ወ.ዘ.ተ.ጉርጓድ ውስጥ አስረው በውሃጥምና በእራብ አሰቃይተው፣እንደውሻ ዱላ ደብድበው በመግደል፡ አለዚየም፡ እንደ ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፡ ታጋዮች በጥይት መረሸን፡ ካልሆነም በማሳሰር፡ ብቻ በሆነ ነገር ኮሎኔሉን ከአካባቢው፡ በማጥፋት እሱ ይምራችሁ የሚለውን ጥያቄ፡ ማንም እንዳያነሳባቸው ማድረግ ስለሆነ፡ ለዚህ ግባቸው መሳካት ደግሞ ውሸት ፈብርኮ ለኤርትራ መንግስት ታደሰ ሊያሰራን አልቻለም፡ በማለት የማያቋርጥ አቤቱታ ማቅረብ፡ ስለነበረባቸው፡ ከእረጅም ጊዜ ጥረት በሗላ እርኩስ ዓላማቸው ተሳክቶላቸዋል።

እስካሁን ግልጽ ያልሆነው ግን ኮሎኔል ታደሰን፡ የኤርትራ መንግስት እራሱ አስሮታል? ወይንስ አሳልፎ ለዚህ ወልዶበላ ድርጅትና፡ ግብዝና መሀይም መሪዎች ሰጥቶታል? የሚለው ነው። ይህነን እርዕስ ለማጠቃለል መነሻዬን ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛልና፡ የመሰወሩ ምክናያቶችስ ምንና እነማን ናቸው፡ የሚለውን ከዚህ በላይ በዝርዝር ለማሳየት ሞክሪያለሁ፡ ጠቅለል አድርጌ ለማስቀመጥ፡ ደግሞ ለዚህ ጀግና እና እውነተኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሰወር፡ መነሻውም መድረሻውም፡ አንድና አንድ ብቻ ነው፡ እሱም በስሟ እየነገደ ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ ብርቅዬ ልጆቿን እንደምስጥ እንክት አድርጎ የበላውና እየበላ ያለው፡ ካልተነቃበት ለወደፊትም ከመብላት የማይገታው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ነው።

ለዛሬ በዚህ ላብቃ ቀሪውን ሳምንት በክፍል3 እመለስበታለሁ ለዚያ ሰው ይበለን ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ አሜን!!!!!

 

 

ስለ ኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል ከፍል 3

ይታያል የሩቅሰው

የክፍል ሁለት መጣጥፌ ያጠነጠነችው፡ የመሰወሩ ምክናያቶችስ ምንና እነማን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ምላሸ በመስጠት ዙሬያ ሲሆን፡ ማሳረጊያየ፡ ለዚህ ጀግና እና እውነተኛ፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፡ መሰወር ምክናያቱ አንድና አንድ ብቻ ነው። እሱም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ።በማለት ነበር፡፡ ወደዛሬው ምልከታየ፡ ለመግባት መንደርደሪያ የማደርገው፡ ደግሞ ተከታዩን ጥያቄ ነው።

3.1. እኛስ ስለ እሱ ምን ብለናል?

ኮሎኔል ታደሰ ሙሉለነህ፡ ከህዝብ እይታ ከተሰወረ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም፡ ከሁለት አመት በላይ እየሆነው ይመስለኛል፡ እኛ ኢትዮጵያውያን፡ወገኖቹስ፡ የት እንዳለ ለማወቅ ወይንም ለማስፈታት ያደረግነው ጥርት ነበረ ወይ? ቢባል በጣም ጥቂት ሰዎች፡ በግል ካደረጉት ሙከራ በቀር፡ እንደህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅእነቱ፡ ታስቦበት፣ በተደራጀና በተቀናጀ፡ መልኩ የተከናወነ ነገር የለም። በተለይ አንጻራዊ ነፃነት ያለው፡ በውጭ ሃገር የሚኖረው፡ ኢትዮጵያዊ አሁንም ሆነ ቀደም ብሎ፡ ወገኖቻችን በታሰሩና በሚታሰሩ ጊዜ፡ በሰላማዊ ሰልፍ፡ የይፈቱልን ጥያቄ እንዳቀረብን ሁሉ፡ የኤርትራ መንግስት አዳመጠንም አላዳመጠን፡ ኤርትራ ሌላ ሀገር ሆናለች፡ እኛ ኢትዮጵያዊ ነን ሳንል፡ ኮሎኔል ታደሰን በተመለከተ፡ የኤርትራ ኢንባሲ በሚገኝበት ሀገር ሁሉ፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና፡ የኤርትራን አምባሳደሮች በማነጋገር፡ በእነሱ በኩል ለሀገሪቷ ፕሪዘዳንት፡ መልእዕክት እንዲደርስ ማድረግ፡ ስንችል አልሞከርነውም።

ጉዳዩ የኢትዮጵያውያንን ስሜት ሳይቆነጥጥና፡ በግልም ሆነ በቡድን፡ ሳይነሳ ቀርቶ ግን አይደለም፡ ኮሎሌል ታደሰ ሙሉነህ፡ከታሰረወዲህ፡በሚደረገው፡ የሃሳብ ልውውጥ፡ ሁሉ ቀድሞውንም ቢሆን ሻብያ፡ ለኢትዮጵያ ነጻነት፡ አስቦ ይደግፈናል፡ ማለት ቂልነት ነው፡ የሚለው፡ ኢትዮጵያዊ በጣም ብዙ እየሆነ ነው። በዚህ ሰው መታሰር ምክናያትም፡ ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፡ ግን በእሱ እስራት እጃቸው የሌለበትን፡ ተቃዋሚወች፡ ሳይቀር በጥላቻ አይን፡ የሚመለከቱና ከመደገፍ የተገቱ፡ ኢትዮጵያውያንም ጥቂት ቁጥር ያላቸው አይደሉም፡ ይህ ጥላቻ አድማሱ እየሰፋና፡ እየከፋ በመሄድ ላይ ስለሆነ በዚያች ሀገር በኩል፡ በሚሞከረው የነጻነት ትግልም ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የሚናቅ፡ አይሆንም የሚል ስጋትም አለኝ። በኮሎኔል ታደሰ መታሰር ዙሪያ፡ በጥልቀት ከሚነጋገሩት፡ ኢትዮጵያውያን፡ ምሁራን መካከል አንዳንዶቹ፡ እንዲያውም ሻብያና ወያኔ፡ ለስልጣን እድሜ ማራዘሚያ፡ ይበጃቸው ዘንድ በሁለቱም ሀገር ህዝቦች ላይ የፖለቲካ ቁማር፡ እየተጫወቱ ነው እንጅ፡ አልተጣሉም፡፡ አሁንም ቢሆን በኤርትራ በኩል የሚንቀሳቀሱ የወያኔ ተቃዋሚዎች፡ በሰላም የሚኖሩት፡ ለወያኔ ስጋት መሆን እስካልቻሉ ድረስ ነው፡ እዚያ የሚደርሱ ከሆነ፡ የሚጠብቃቸው የእነኮሎኔል ታደሰ እጣ ፋንታ ነው። ጸባቸው ከምር ቢሆን ኖሮእማ፡ ወያኔ በባድመ ጦርነት ወቅት፡ ሻብያን መደምሰስ ከሚያስችለው ደረጃላይ ሲደርስ፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠር፡ ኢትዮጵያዊ፡ ሻብያ በቀበረው ፈንጅ ላይ እንዲረማመድ በማድረግ፡ ካስጨረስ በሗላ፡ የሻብያን መሸነፍ ሲያይ፡ ውጊያው እንዲቆም ባላደረገና፡ የዚያ ሁሉ ህዝብ እልቂት ምክናያት የሆነችውን ባድመንም በድርድር ሰበብ አሳልፎ፡ ለኤርትራ ባልሰጠ ነበር፡፡

ሻብያም በፋንታው፡ ወያኔ እንዲጠፋ ቢፈልግ ኖሮ፡ በኤርትራ ውስጥ በእየቀኑ እንደዶሮ ጫጩት በመፈልፈል፡ የብሄር ጎጆ ቀልሶ የሰፈረውን፡ ተቃዋሚ ወይ ተባበሩ፣ እንቢ ከአላችሁ ደግሞ ከሃገሪ ውጡ በማለት፡ በግድም፣ በውድም ወደ አንድነት፡ እንዲመጣ አድርጎ፡ ቢያሰልፍው ወያኔ በአጭር ጊዜ ያልቅለት ነበር፡ ወ.ዘ.ተ. የሚሉ መከራከሪያወችን አጽኖት ሰጥተው ያቀርባሉ።

እኔን እንደሚመስለኝ ግን፡ የሻብያና የወያኔ ጸባቸው የእውነት ነው፡ የዛሪ መነጋገሬያችን ሻብያ ስለሆነ፡ የወያኔን አመለካክት ላቆየውና፡ በተለይም ሻብያ፡ ወያኔ እንዲወገድ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ ግን በሻብያ እምነት፡ ከወያኔ ውድቀት በሗላ የምትመሰረተዋ፡ ኢትዮጵያ በምንም አይነት፡ መንገድ፡ ለኤርትራ ስጋት የማትሆንበትን ሁነኛ ማረጋገጫ መገኘት አለበት፡፡ ወይንም ስጋት በማትሆንበት መልክ መዋቀር መቻል አለባት። ያ እስኪረጋገጥ ግን ሻብያ፡ ከወያኔ የባሰ ጠላት እንዳይመጣበት ሰለሚፈራ እራሱ ወያኔ ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ ይፈልጋል።

እራሴን በሻብያ ባለስልጣናት ቦታ አስቀምጨ ሳየው፡ ይህ ስሌታቸው፡ ትክክልም የሚሆንበት፡ እውነት አለው፡፡ ምክናያቱም አንድ ሀገር በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሀገር፡ ለመቀጠል ሀቀሟ የፈቀደላትን ሁሉ በማድረግ፡ የስጋት ምንጯን ማድረቅ፡ አለባት። ለኤርትራ ደግሞ ከአጎራባቾቿ ሀገራት መካከል፡ ስጋቷ ኢትዮጵያ ብቻ ነች። መንስኤውም፡ሌላ ሌላውን እንተወውና፡ የኢትዮጵያ፡ ታሪካዊይም፣ ህጋዊየም፡ አካሏ የሆነውን አሰብን፡ ያለህግ አግባብ፡ በወያኔ እንደተቸራት፡ ታውቃለች። ወሎ ይደር እንጅ ኢተዮጵያዊ ፡መንግስት በመጣ ጊዜ፡ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ የባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄን፡ ማንሳቷ የማይቀር መሆኑን፡ ኤርትራ በሚገባ ትገነዘባለች። ይህነን ስጋቷን በማያጠራጥር መልኩ ለማስወግድ፡ ግን ብዙ መስራት ስለሚጠበቅባት፡ በጥንቃቄ እየሄደችበት ነው፡ በበኩሌ ያለውን ተጨባጭ እውነታ፡ እስካሁን እያደረገችው ካለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር በማዛመድ፡ ሳየው ኤርትራ፡ ስለ ኢትዮጵያ ሶስት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን፡ የምትከተል ይመስለኛል፡፡

እነሱም

1ኛ/ እንደጎርቤት ሀገር ሶማልያ፡ ስራት አልበኝነት የሰፈነባት ያለመንግስት የምትኖር ሀገር እንድትሆን፡ በማድረግ፡ ስጋትነቷን ከማስወገድም ባሻገር፡ ያለከልካይ፡ በፈለገችው ጊዜና በሚያስፈለገው አካበቢ በመግባት፡ጥሪ ሃብቷንና የጥሪት ክምችቷን፡ በመውሰድ፡ ስትጠቀም መኖር።

2ኛ/ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ጠፍታ ቐንቐን መሰረት ባደረጉ፡ በርካታ መንግስታት፡ እንድትከፋፈል፡ በማድረግ፡ አሁን በወያኔ እንደሚፈጸመው፡ ለስሙ በመሪነቱ ቦታ ላይ ኤርትራ ውስጥ የሚኖሩና በብሄር የተደራጁ፡ ተቃዋሚዎች እንዲቀመጡ፡ ተደርጎ፡ ቁልፍ ቦታዎች፡በሻብያ ካድሬዎች እንዲያዙና፡ ከአስመራ፡ በሚተላለፍ፡ ቀጭን ትእዕዛዝ፡ በእጅ አዙር ቅኝ፡ የምትተዳደርና ለኤርትራ ስጋት እነቷ ያከተመላት፡ እንድትሆን ማድረግ፡፡

3ኛ/ ሁለቱ ካልተሳኩና የአንድነት ሃይሉ ከአየለ፡ በምንም መንገድ ይሁን፡ ተስማምቶ መልካም ጎረቤት በመሆን መኖር፡ የሚሉት ናቸው።

ስለዚህ እቅድ አንድና ሁለት፡ ተሞክረው፡ አለመስራታቸው ሳይረጋገጥ፡ እንደ እነ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ አይነት፡ በጽኑ ኢትዮጵያዊነት የሃገር ፍቅር የተጠመደ፣እንዲሁም፡ ሁለንተናዊ፡ የማድረግ አቅሙ ያለውን፡ ዜጋ ማበረታታት፡ ለዓላማቸው መሳካት የማይመች ስለሚሆን፡ ይህንን ሰው፡ ገለል እንዲል ማድረጉ፡ የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ከሀገር እንዲወጣ፡ ማድረግ እንጅ፡ በፈቃድ የገባን የሌላ ሀገር ዜጋ፡ ለዚያውም

ከአንድ ሃገር ዲፕሎማት፡ የማይተናነስ ህዝባዊ እውቅና ያለውን ሰው፡ ማሰር ተገቢ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፡ የኢትዮጵያን ህዝብ መናቅና፡ የፖለቲካ ጥበብም የጎደለው ነው ባይ ነኝ። ሌላውና የሚያሳዝነው ደግሞ፡ የጎዳኝ የእኔው ጠማማ ነው፡ አለ እንደሚባለው እንጨት፡ እንደ አለመታደል ሆኖ፡ የሻብያን የጥርጣሪ ክብሪት የጫሩትና፡ እንዳይጠፋም፡ በተከታታይ ቤንዚን በማርከፍከፍ እዚህ ደረጃ ያደረሱት፡ የእራሳችን ሰዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው።

ሻብያስ ቢሆን፡ እንዴት የአስተዳድርና፡ የዲፕሎማሲ ጥበብ የሚባል ነገር አይታየውም? ኮሎኔል ታደሰን፡ እኮ በምርኮ አልያዘውም፡ ለምኖና ሊያታግለው፡ ቃል ገብቶለት ነው ወደ ሀገሩ ያስገባው፡ ከገባም በሗላ ብዙ ሰዎቹን፡ በተዎጊ ጀት አብራሪነት፡ ያሰለጠነ፡ ባለውለታው ነው፡፡ እንኳን መንግስትን ያህል ተቋም ይቅርና ግለሰብ እንኳን ቃሉን ያከብራል፡ ይህ ሰው እንኳን ያላጠፋውንና ቢያጠፋና፡ ሺህ ክስ ቢቀርብብትም፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከረሁት፡ ቃል ገብቶ እንዳስገባው ሁሉ በሰላም፡ ከሃገር እንዲወጣ ይደረጋል እንጅ፡ እንዴት ይታሰራል? የኤርትራ መንግስትስ እንዴት ቃሉን ይበላል? ወደፊት ለሁለቱ ሃገር ህዝቦች፡ ግንኙነትስ እንዴት አያስብም? ነው ወይንስ ከምር ወደፊት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳትኖር ማድረግ እችላለሁ፡ ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ፡ ይሆን?

ይህ ጥያቄ ሁል ጊዜ በሃሳቤ ይመላለሳል፡ በዚህ አጋጣሚ እስኪ የግል ምኞቴን ላስቀምጥ፡

ሻብያዎች 1ኛወንና 2ኛውን፡ የፖሊሲ አቅጣጫ፡ እንደ ቀን ቅዠት ቆጥረው በማለፍ፡ 3ኛው ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው። ምክናያቱም፡ በጦርነት ማንም ያሸንፍ ማን አሸናፌም፣ ተሸናፌም፣ የሚደርስባቸው ሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ለሁላችንም የሚበጀው ሰላሙ ሰለሆነ፡ ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ።

ወደ መነሻዬ ልመለስና፡ ላጠቃለው፡ በፊት የተናገረን፣ ሰው ይጠላው፡ በፊት የደረሰን ሰብል ወፍ ይበላው፡ እንዲሉ ሆኖ እነኮሎኔል ታደሰ፡ ቀድመው በመገኘታቸው፡ የችግሩ ግንባር ቀደም፡ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። እኛ ኢትዮጵያውያንም፡ እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ በአይናችን እያየን፣ በጆሮአችን እየሰማን፡ ብዙ ማድረግ ስንችል፡ ምንም ነገር ሳንሞክር፡ ዝም ብለን ተቀምጠናል። ለጽሁፌ፡ መግቢያ ለአደረግሁት፡ እኛስ ምን ብለናል፡ ለሚለው ጥያቄ መልሱ፡

አልናገርም እንዲያው ዝም ጥርቅም፡

ጊዜ የሚወልደው አይታወቅም።

እንዳለው ሟቹ አርቲስት ይርጋ ዱባለ፡ ዝም ጥርቅም ብለናል የሚለው ነው። ድርጊቱ በወያኔ የተፈጸመ ቢሆን እንኳ፡ ጊዜ የሚወልደውን ብንጠብቅ ጥቂትም ቢሆን ተገቢነት በኖረው ነበር፡ በሻብያ በኩል ግን ጊዜ የሚወልደው አጋጣሚ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ላይ ሁነን ልናከናውነው የምንችለው፡ብዙ በጣም ብዙ ነገር እያለ፡ ዝም ማለታችን፡ አሳዛኝም አሳፋሪም ነገር ነው። ለመሆኑ ለትናንት ጀግኖቻችን፡ ስራ እውቅና ካልሰጠን፡ ለዛሪ ጀግኖቻችን፡ በችግሮቻቸው ካልደረስንና፡ ገድላቸውን በመተረክ፡ አርያነታቸውን አጉልተን ለተተኪው ትውልድ ካላሳየን፣ እንዴት ነው ለወደፈት ሀገርን ከጥፋት ህዝብን ከውርደት፡ ሊታደግ የሚችል ጀግና የምናፈራው? የምንተካውስ??

 

ሳምንት በመሰናበቻ ቅኝቴ እስክመለስ ለዛሪን አበቃሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ አሜን!!!!

ሀምሌ ወር 2005 ዓ.ም