“አማራውን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ልሂቃን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ማጋጨት የታክቲክም የስትራቴጂም ጥቅም የለውም” ☞[ፈቃደ ሸዋቀና] #ነፃነት

ኢዲተር፣ አቶ ፍቃደ ሸዋቀና ሕወሃት ስልጣን በተቆናጠጠ ማግስት ከአማራ ብሄር በመሆናቸው ብቻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት ከ40 በላይ መምህራን ውስጥ አንዱ ናቸው።
ፈቃደ ሸዋቀና
እስቲ አሁን ይህን ምን ይሉታል? እኔ ፕሮፌሺናል የታሪክ ተማሪ ወይም ምሁር አለመሆኔን ተናገርኩ። መሳሳት የምችል መሆኔንና በዚህም ሰው እንዳይፈርድብኝ መጠንቀቄ ነው። ይህ ማለት መቼም ምንም የኢትዮጵያ ታሪክ አላውቅም አላነበብኩም አልተማርኩም አልሰማሁም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ አካዳሚያ ውስጥ ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ። እንዴውም በተለይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሳለሁ የነበረኝን እድል አስታውሼ ከብዙ ትልልቅ የታሪክ ምሁራን ጋር ቅርብ መሆኔን ጠቀስኩ። እንደ ፕሮፈሰር መርድ ወልዳረጋይ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ የመሳሰሉ ግዙፍ የታሪክ ሰዎች ጋር ሻይ ላይ እንደኔ ለአመታት ሳይሆን እንድ ሰዓት አብሮ ተቀምጦ ታሪክ ማወራት ትልቅ ትምህርት ነው። ብዙ ጊዜ እወርተን ብቻ ሳይሆን የሚነበቡ መጻህፍትና ለራሴም የምሞክረው የምርምር ርዕስ ሁሉ ጠቁመውኝ ያውቃሉ። እኔ ህይወት አጋጣሚ ፈጥሮልኝ ክንደዚህ አይነት ምሁራን ጋር ውዬ ጉዋደኛ ሆኘ ብዙ ተምሬያለሁ ያልኩት የታሪክ ፕሮፌሽናል ባልሆንም ብዙ ነገር መማሬን ለማስታወስና በማላውቀው ነገር ላይ የምዘባርቅ ሰው አለመሆኔን ለመጠቆም ያህል ነበር።
ለዚህ የተስጠኝን ያቶ ሄኖክ የሺጥላን የሽሙጥና ስድብ መልስ ተመልከቱ።
<<ታሪክ አላውቅም ከታሪክ ሙሁሮች ጋር ግን እውል ነበር » ከሚል ምሁር ይጠብቃችሁ። ለኔ እንዲህ አይነቱን ምሁር ኩራዝ ያዥ ምሁር እለዋለሁ። በልቼ አላውቅም ሲበሉ ግን ቁሜ አበላ ነበር እንደማለት ነው ። ኖሬ አላውቅም ሲኖሩ ግን አይቻለሁ፥ ተናግሬ አላውቅም ሲናገሩ ግን ሰምቻለሁ፥ አስቤ አላውቅም ሲያስቡ ግን አይቻለሁ። ምንድን ነው ሃሳብ ሰንዝሮ ከመሞገት ፥ ሲባል አልሰማሁም የሰማችሁ ካላችሁ ንገሩኝ ብሎ ማለት ? ከታሪክ ምሁራኖች ጋ ለብዙ ጊዜ ሻይ ጠጥቼያለሁ ፥ ሆኖም ግን አንድም ቀን ይህንን ታሪክ በተመለከተ ሻይ ላይ ሲወራ ሰምቼ አላውቅም !? Really ? ብዙ የታሪክ ምርምር እና ጥሁፎችን ታቀረቡ ሰዎች ጋር አብሬ ነበርሁ ፥ ይህ ሲባል ግን ሰምቼ አላውቅም ! አሁን ይሄ መልስ ነው ጥያቄ ? ፍሬ ነገሩ ምንድን ነው? ልክ አይደለም ማለት አልችልም ፥ ግን ደሞ ልክ አይደለም ፥ ምክንያቴ ደሞ የማውቀው ነገር ስላለ ሳይሆን ሲባል ሰምቼ ስለማላውቅ ! «ሲነገር ሰምቼ አላውቅም ስለዚህ ተናጋሪ አለመኖሩን ዋቢ ማስረጃ አድርጌ የተባለው ያልነበረ ነው ለማለት እችላለሁ» ምን አይነይ መደምደሚያ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ትሪልየን ዶላር ያለው ግለሰብ አለ ሲባል አልሰማሁም ፤ ከብዙ ባንከሮች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግሬያለሁ ስለዚህ ትሪሊየን ቁጥር ነው ብዬ ለማመን ይከብደኛል! እንደማለት እኮ ነው !!!! ለማንኛውም ለምሁራችን እንደ ማሟሟቂያ የአባ ባህሪን ድርሰቶች ለምን አንጋብዘውም ! ዋን ፎር ዘ ሮድ ! ለታሪካዊ ማብራሪያው እንመለስበታለን !”>>
እንዲህ አይነት እብሪት ከየት እንደሚመጣ ለመገመት ያዳግታል። አቶ ሄኖክ አንድን ነገር በግጥምና በተቀሸረ አማርኛ ስለተናገረው እውነት የተናገረ የሚመስለው ሰው ይመስለኛል። እኔ ያውም በሚያገባኝ ነገር ማንንም በስርዓት የመተቸት መብት አለኝ ብዬ አምናለሁ። በመሰረቱ ለተሳዳቢዎች ከፍተኛ ንቀት ስላለኝ አያናዱኝም። ሶሻል ሚዲያ ላይ ተሰደብኩ ብሎ መናደድም ቂልነት ነው። ግፋ ቢል ይበልጥ እንድንቃችሁ ታደርጉኝ እንደሆን እንጂ አትጎዱኝም። እኔን በመስደብ ደስታ የምታገኙ የመሰላችሁ መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ። ብዙ ሰው የክርክሩ መላ ሲጠፋው ወደ ስድብ እንደሚሄድም አውቃለሁ።
እኔ ያማራ ህዝብ መደራጀት ተቃዋሚ አይደለሁም። ራሴ በወያኔ መንግስት ባማራነት ጥቃት ከደረሰባቸው ከመጀመሪያዎቹ አማሮች ውስጥ ነኝ። ዘመኑ ወያኔ መጀመሪያ ጎሳዬን ከዚያ ኢትዮጵያዊ ነኝ በሉ የሚል ከረጢት ውስጥ ሊያስገባን ብዙ የሚደክምበት ጊዜ ነበር። እኔ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ከወረድኩ አፍሪካዊ እሆን እንደሆን እንጂ ጎሳ ከረጢት ውስጥ እልገባም አልኩ። ዛሬም አማራነቴና ኢትዮጵያዊነቴ ተሙዋግተውብኝ አያውቁም። ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ውስጥ ሆኘም ሆነ በግሌ አማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ታግያለሁ። እየታገልኩም ነው። ከማንም ባልተናነሰ።
እንደ አንድ አማራ አማራነት መነገጃ ሲሆን፣ ያማራ ህዝብና ወጣቶች ወደ አደገኛ አቅጣጫ ሲገፉ፣ ራዕይም ዶክትሪንም ስትራቴጂያዊ አስተሳሰብም የተራቆተ ፖለቲካ ውስጥ እየተጎተቱ እንዲማገዱ ሲጋበዙ ግን ዝም ብዬ አላይም። በደልንና ጥቃትን ብቻ በማውራት በተለይ ወጣቶች በቁጭት ተነስተው ወደ ተራ መንጋነት እንዳይቀየሩ ላማራ ህዝብ ትግል የሚያደርጉት ድጋፍም ተሳትፎም ዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እመክራለሁ። በተለይ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ልሂቃንም ይሁን ሌላ ድርጅቶችና ተቋሞች ጋር አማራን ለማጣላት የሚደረገው የነጋዴ ፖለቲካ የታክቲክም የስትራቴጂም ጥቅም የሌለው በሌሎች ኪሳራ ለመነገድ የሚደረግ የነጋዴ ፖለቲካ መሆኑን ለማስተማር አሞክራለሁ። ወይም ለስማቸው መጠሪያ ቁና ሊሰፉበት የፈለጉ ጀብደኞች አላማ ያልበለጠ ነገር መሆኑን እንደሽንኩርት እየላጥኩ ለማስረዳት እሞክራለሁ። በህር ማዶ ቁጭ ብሎ እግር ዘርግቶ ተቀምጦ በየለቱ የሚማገዱ ሰዎችን አላማ ለማጣመምና ከወዳጅ ይልቅ ጠላት እንዲበረክት ሊደረግባቸው ሲሞከር እያየን ማንኛችንም ዝም ልንል አይገባም።
አቶ ሄኖክ ያባ ባህርይን ድርሰት የታሪክ መጽሀፍ አድርጎ የወሰደው ይመስለኛል። ያባ ባህርይ ድርሰቶች ድንቅና በጨለማ ዘመን ሬከርድ ላይ የሰፈሩ ብዙ ነገሮች ላይ ብርሐን የፈነጠቁ የታሪክ መረጃዎች እንጂ በራሳቸው ታሪክ አይደሉም። ታሪክ እንዲሆኑ ታሪክ ጸሀፊዎች ከሌሎች ታሪክ መረጃዎች ጋር በማጣመር ሊመለከቱዋቸውና ሊያረጋግጧቸው ይገባል። የነገስታቱን ታሪክ ክሮኒክለሮችና የባለሙዋሎቻቸውን ማስታዎሻዎች ሁሉ ታሪክ ጸሀፊዎች የሚያዩት እንደዚህ ነው። የተጻፈን ነገር አንጠልጥሎ መሮጥ ሁሉ ታሪክ አዋቂ አያደርግም። በጥንት ጊዜ አማሮች ታቦት ይዘው ገዳም መስርተው ጥቂት ሆነው በየቦታው ይኖሩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ይህ ምናልባት በማህበረሰብ ደረጃ በዚያ አካባቢ ይኖሩ እንደነበረ ያሳይ እንደሆን እንጂ የሀገሩ ገዥዎች እነሱ እንደነበሩ አይመሰክርም። አባ ባህርይ አማሮች ይኖሩበት ነበር ያሉት ቦታ ሁሉ ግዛታቸው ነው አለማላታቸው መሆኑን ማወቅም ጥሩ አንባቢ መሆን ነው።
ክርክር እዋቂ ያደርጋል እንጂ ሰው እይገልም፣ አያቆስልም። የማያውቁትን ነገር መጠየቅ አዋቂነት እንጂ ነውር አይደለም። ስድብ ደግሞ የድንቁርና መግለጫ ነው። በስልጡን መንገድ ዱላ ቀረሽ ክርክር ማድረግ ይቻላል። እኔ እንደዚህ አይነት ክርክር enjoy አደርጋለሁ። ያማራ ህዝብ ችግሮች ደግሞ የጥሞና ውይይቶች፣ የበሰሉ ክርክሮችና በጥልቀት የታሰበባቸው ስትራቴጂዎችና ተወዳዳሪም ቢሆኑ የሚመጥኑት ራዕዮች ያስፈልጉታል። ከሁሉ በላይ አሁን ብዙ አማሮች ለነጻነታቸው ለመጋደል በመረጡበጥ ሰዓት መሰማራት ያለብን ወዳጅ ስብሰባ ላይ እንጂ ጠላት ፍለጋ ላይ መሆንና ሌሎች ላይ ማቅራራት መሆን የለበትም። ያማራ ህዝብ ጠላቱ ያገዛዝ ስርኣቱ ብቻ ነው፡፡

Image may contain: one or more people, people standing, grass, outdoor and nature